==
መንኸፐሬ 3 ቱትሞስ | |
---|---|
የ3 ቱትሞስ ሐውልት | |
የግብጽ ፈርዖን | |
ግዛት | 1466-1433 ዓክልበ. |
ቀዳሚ | ሃትሸፕሱት |
ተከታይ | 2 አመንሆተፕ |
ባለቤት | ሳቲያሕ፣ መሪትሬ-ሃትሸፕሱት፣ ነብቱ፣ መንዊ፣ መርቲና መንኸት |
ሥርወ-መንግሥት | 18ኛው ሥርወ መንግሥት |
አባት | 2 ቱትሞስ |
==
መንኸፐሬ 3 ቱትሞስ በጥንታዊ ግብጽ የግብጽ አዲስ መንግሥትና የ18ኛው ሥርወ መንግሥት ፈርዖን ሲሆን ምናልባት 1466-1433 ዓክልበ. የገዛ ነበረ።
የአባቱ 2 ቱትሞስ ቁባት ንግሥት ኢሰት ተባለች፣ እርሷም የ3 ቱትሞስ እናት ሆነች። የ፪ ቱትሞስ ተከታይ በይፋ ልጁ ፫ ቱትሞስ ሲሆን፣ እሱ ግን ገና የ 2 ዓመት ሕጻን ልጅ ሆኖ በ1487 ዓክልበ. የ፪ ቱትሞስ ሌላ ንግሥት ሃትሸፕሱት ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴው፣ በቅርብም ጊዜ ውስጥ በራስዋ መብት ፈርዖን ተባለች። በአንድ ጽላት ሃትሸፕሱት በየካቲት 10 ቀን፣ 22ኛ ዘመነ መንግሥትዋ (1466 ዓክልበ. ግ.) አረፈች የሚል ነው። ይህም መንኸፐሬ ፫ ቱትሞስ ፈርዖን የሆነበት ቀን ነበር፣ ሆኖም በተመሳሳይ እንደ 22ኛ ዘመነ መንግሥቱ ይቆጥሩት ነበር።
ስለ፫ ቱትሞስ ዘመቻዎች የሚገልጹ ከዘመኑም የሆኑ በርካታ ምንጮች ተገኝተዋል። ግዛቱን ከናፓታ በደቡብ (የኩሽ መንግሥት መርዌ ዋና ከተማ) እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ በስሜን ድረስ በ17 ዘመቻዎች አስፋፋው።
በየካቲት 10 ቀን 1466 ዓክልበ. ብቸኛው ፈርዖን እንደ ሆነ ወዲያው ሥራዊቱን ይዞ በመርከብ በሶርያ ደርሶ ዘመተ። ይህ ሶርያዊ ዘመቻ ከመጊዶ ውጊያው ዘመቻ ፪ ወር በፊት እንደ ሆነ በአርማንትና በናፓታ በተገኙት ጽላቶች ይገለጻል፤ በመካከሉ ወደ ግብጽ ቢመለስም ሁለቱም ግን «መጀመርያው ዘመቻው» ይባላሉ።
በናፓታ ጽላቱ ላይ ቱትሞስ እንዲህ ይላል፦ «ግርማዊነቴ ወደ ስሜን ወደ እስያ ዳርቻ በመርከብ ሄድኩ። በጌባልም ግርማዊነቴም ብዙ የአርዘ ሊባኖስ መርከቦች ወደ ጋሪዎች ታስረው በበሬዎች ተስበው ከኔ በፊት ወደ ናሓሪን ወንዝ ተጓዙ፣ ወንዙን እንዲሻገሩ።» የቱትሞስም ሥራዊት ኤፍራጥስ ወንዝን ተሻግሮ ወደ ሚታኒ ግዛት ገብተው የሚታኒ ኃያላት ሸሹ ይላል። ከዚያ ቱትሞስ ለግብጽ ይግባኝ የሚል ሐውልት እዚያ በኤፍራጥስ ዳር አቆመ። የአርማንትም ጽላት ደግሞ ይህን ይጠቅሳል። ሁለቱም ጽሁፎች ደግሞ ቱትሞስ በኒያ አገር ሲመለስ 120 ዝሆኖችን አድኖ ገደላቸው በማለት ይስማማሉ። በአርማንት ጽላትም ዘንድ ሰባት አናብስትና 12 ጎሽ ደግሞ እንደ ገደላቸው ይጨምራል።
ይሄው «ኒያ አገር» ያንጊዜ በኢድሪሚ ግዛት (ሙኪሽ)፣ ሚታኒም የባራታርና ግዛት እንደ ነበሩ ይታሥባል። የኢድሪሚም ሆነ የባራታርና መዝገቦች ስለ ግብጽ ቢጥቀሱ ገና አልተገኙም። አንዳንድ ሥፍራዎች ከማቃጠልና ከመዝረፍ በቀር፣ የቱትሞስ ሥራዊት በዚህ ጉዞ ላይ ትልቅ ውጊያ እንዳላገኙ ይመስላል። በሚቀጥለው ዓመት ግን ኢድሪሚ የባራታርና ጥገኛ ተባባሪ እንደ ሆነ ይታወቃል። በ፫ ቱትሞስ መዝገቦች ዘንድ በኤፍራጥስ ላይ ሳለ የኬጥያውያን መንግሥት፣ የአሦርና የባቢሎን (ካሣዊ) ነገሥታት ሁላቸው የግብጽ የበላይነት ተቀብለው የግብር ስጦታዎች ላኩለት ይባላል። «ዘጠኙ ቀስቶች» ወይም ክግብጽ ስሜን ባሉት ደሴቶች (እነ ቆጵሮስ?) ደግሞ በቱትሞስ ግዛት ውስጥ ነበሩ ብሎ ይግባኝ አለ። ሚታኒ ብቻ ለግብጽ የማይገብረው ኃይል ቀረ ማለት ነው።
ቱትሞስም ከዚህ በኋላ ከኒያ አገር ወድ ግብጽ ገሥግሦ ተመለሰ። በከነዓን ምድር (ግብጽኛ፦ ጃሂ) ሲያልፍ፣ ኗሪዎቹ ባብዛኛው ፈርተው እቤቶቻቸው ውስጥ ተደበቁና ቱትሞስ የግብጽ ይግባኝ ማለቱን በዚህም ጣለ ይላል። ሆኖም በመጊዶና በተለይ በቃዴስ (ግብጽኛ፦ ረጨኑ) የተገኙት ከነዓናውያን ተሰብስበው እንደ ተቃወሙት ተመለከተ። በመጽሐፈ መሳፍንት መሠረት ዕብራውያን በዚህ ዘመን በጎቶንያል ፈራጅነት ነበሩ፤ በጎቶንያል ሥር አርባ አመት ሰላም አገኙ ከማለት በቀር ስለ ግብጾች ይሁንና ምንም ሌላ መረጃ አይሰጥም። ከጊዜ በኋላ በፈራጆቹ ዘመን የዕብራውያን ማዕከል በገለዓድ ወይም ከዮርዳኖስ ወንዝ ምሥራቅ ሙሴም ባሸነፈው ምድር መሆኑ ይመስላል፤ ምናልባት በጎቶንያል ዘመን ደግሞ የእስራኤላውያን ቅሬታ የተገኘው በተለይ በዚያ በገለዓድ አገር እንደ ሆነ ይቻላል። የሻሱ ወይም ሱቱ ሕዝብ በኤዶምና ሞአብ ብቻ ሳይሆን ከዮርዳኖስ ምዕራብ ደግሞ ይጠቀሳሉ። መጽሐፈ መሳፍንትም እንደሚለን የከነዓን ወገን በባሕር ዳር ላይና በተለይ በመጊዶ አካባቢ ቀርተው ነበር።
ወደ ግብጽ ተመልሶ ወዲያው በሚያዝያ 25 ቀን ቱትሞስ ዞር ብሎ ከ10 ወይም 20 ሺህ ጭፍሮች ጋር ወደ ስሜኑ ገሠገሠ። «እንዲህም ሆኖ ነበር፤ በሻሩሄን የነበሩት ነገዶችና ሕዝቦች፣ ከያራዛ (ኢየሩሳሌም?) እስከ ዓለሙ አሮንቃ (ኤፍራጥስ) ድረስ በጊርማዊነቱ ዓምጸው ነበር።» በግንቦት 4 ቀን ወደ ጋዛ ደረሰ፣ ይህም ከዚያ በፊት የግብጽ ከተማ ነበር። በግንቦት 5 ቀን ከጋዛ ለዘመቻ ወደ ረጨኑ ወጣ።
በመንገዱ ላይ ወደ ኢዮጴ ከተማ መጣ። በአንዱ ጽሑፍ ዘንድ፣ ኢዮጴ ለፈርዖን ጠላት ሆኖ የግብጽ የጦር አለቃው ጀሁቲ 200 ሰዎች በማቅ ውስጥ ደብቆ እንደ ስጦታ አስመስሎ የኢዮጴም ሰዎች በከተማው ግድግዶች ውስጥ አስገብተዋቸው ከተማውን መያዝ ተቻሉ። የዛሬው ታሪክ መምኅሮች ይህንን ጽሑፍ ልቦለድ ብለውታል፤ ሆኖም የጦር አለቃው ጀሁቲ መቃብርና ቅርሶች ከ1816 ዓም ጀምሮ ለሥነ ቅርስ ታወቀዋል። በባሕር ዳር መንገድ ተቀጥሎ በግንቦት 16 ቀን በየሄም ደረሰ፣ የሄምን ከመጊዶ የሚለዩም ተራሮች አሉ። በግንቦት 19 ቀን ሥራዊቱ በመጊዶ አጠገብ ባለው ሜዳ ደረሰ። የረጨኑም ሥራዊት በቃዴስና በመጊዶ ነገሥታት ተመራ። በግንቦት 21 በረጨኑ ሥራዊት ላይ ጥቃት ጥለው ግብጻውያን በመጊዶ ውግያ አሸነፉዋቸው፤ የረጨኑ ቅሬታ ግን ወደ መጊዶ ከተማ መሸሽ ቻሉ። የረጨኑ ሰዎች እጅ እስከሚስጡ ድረስ ግብጻውያንም ለሰባት ወር ከበቡዋቸው። ከተማረከው ሀብት ብዙ ብር፣ ወርቅ፣ ዕንቁ፣ እኅል፣ ወይን ጠጅ፣ 340 ምርከኞች፣ 2041 ባዝራዎች፣ 191 ፈረስ ግልገሎች፣ 6 ድንጉላ ፈረሶች፣ 2 የወርቅ ሠረገሎች (የነገሥታት) ፣ 924 ሠረገሎች ባጠቃላይ፣ 2 የነሓስ ጥሩሮች (የነገሥታት)፣ 200 ጥሩሮች፣ 502 ቀስቶች፣ 7 የብር ድንኳን ዓምዶች፣ 1929 ትልልቅ ከብት፣ 2000 ትንንሽ ከብት፣ 20500 ነጭ ትንንሽ ከብት (በግ) ወሰዱ። ከዚህ በኋላ ቱትሞስ ወደ ደቡብ ሊባኖስ ገሥግሦ ሦስት ከተሞች ይዞ በዚያ መካከል የግብጻውያን አምባ አሠራ፤ ከዚህም አገር የዘረፈው ዝርዝር 2503 ሰዎች፣ ብዙ የድንጋይና የወርቅ ዕቃዎች፣ የሐቢሩ ዕደ ጥበቦች፣ 3 ትልልቅ ጀበናዎች፣ 87 ቢላዋዎች፣ ብዙ የወርቅና የብር ቀለበቶች፣ የብርና የወርቅ ሐውልቶች፣ ከወርቅ፣ ዝሆን ጥርስ፣ ዞጲ፣ እና ካራቦ ዕንጨት የተሠሩ ስድስት ወምበሮች፣ 6 የግርም መቀመጮቻቸው፣ የዞጲ፣ ወርቅና ዕንቁ ሐውልት፣ የነሐስ ዕቃዎች፣ ብዙ ልብስም ነው።
የሚከተሉት ጥቃቅን «ዘመቻዎች» ግብር ለመቀበል ብቻ ነበሩ። በ1463 ዓክልበ. በከነዓን ምድር የተገኙት እንስሶችና ዕጽዋት ተዘረዘሩ። በ1459 ዓክልበ በአምስተኛው ዘመቻ በፊንቄ በመርከብ ደርሶ ኡላዛን ወደብ ከቱኒፕ፣ እንዲሁም አርዳታን ያዘ። የሐቢሩም ወገን ሰዎች በኡላዛ ውስጥ እንደተገኙ ግብጾቹ ዘገቡ። በ1458 ዓክልበ. በቃዴስ ላይ ዘምቶ ጹሙሩን (ሰማሪዎን) ወደብና እንደገና አርዳታን ያዘ። በ1455 ዓክልበ. በ8ኛው ዘመቻ እንደገና በሚታኒ ላይ ተዋጋ። በ1454 ዓክልበ. ቱትሞስ ኑሐሼን (በሙኪሽ ግዛት) ዘረፈ። ልዑል ታኩ የኑሐሼ አገረ ገዥ እንዲሆን አደረገው። በ1453 ዓክልበ. የግብጽና የሚታኒ ሥራዊቶች ከሐለብ ስሜን ተጋጥመው ቱትሞስ በአርዓና ውጊያ አሸነፋቸው። በ1452-1450 ዓክልበ ቱትሞስ በኑሐሼ ዙሪያ ይዘምት ነበር፣ አላላኽም (ሙኪሽ) እንኳን ገበረለት።
በ1449 ዓክልበ. ቱትሞስ በሻሱ ብሔር ላይ ዘመተ። ይህም እስራኤላውያን ለሞአብ ንጉሥ ኤግሎም የተገዙበት ዘመን ይመስላል። በ1446 ዓክልበ. ሚታኒ እንደገና በሶርያ ግዛቶቹ መሃል አመጽ አነሳስቶ፣ ቱትሞስ ተመልሶ አርቃን ወደብ፣ ቱኒፕንም ከተማ ያዘ፣ በቃዴስም ዙሪያ ፫ የሚታኒ አምባዎች አጠፍቶ ወደ ግብጽ ተመለሰ። ከዚህ በኋላ በኖቢያ ዘመተና ናፓታን በ1436 ዓክልበ. ያዘ።
የቱትሞስ ዘመቻዎች በካርናክ «የዜና መዋዕል አዳራሽ» በተባለ ሕንጻ በግብጽኛ እንዲህ ተቀርጸዋል፦
ዓመት | ድርጊት ማጠቃለያ |
---|---|
22–23 (1466-65) | 1. ዘመቻ በመጊዶ |
24? (1464) | 2. ፍተሻ ዘመቻ በከነዓን |
25? (1463) | 3. ዘመቻ በረጨኑ |
26? (1462) | 4. ዘመቻ |
29 (1459) | 5. ዘመቻ በፊንቄ |
30 (1458) | 6. ዘመቻ በቃዴስ |
31? (1457) | 7. ዘመቻ በኡላዛ በፊንቄ |
33? (1455) | 8. ዘመቻ በሚታኒ በሶርያ |
34? (1454) | 9. ዘመቻ በሦስት ስሜን ሶርያ ከተሞች |
35 (1453) | 10. ዘመቻ በሚታኒ በሶርያ፣ አሩና |
36? (1452) | 11. ዘመቻ |
37 (1451) | 12. ዘመቻ |
38? (1450) | 13. ዘመቻ በ ስሜን ሶርያ |
39 (1449) | 14. ዘመቻ በደቡባዊ ሻሹ ዘላኖች |
40 (1448) | 15. ዘመቻ |
42 (1446) | 16. ዘመቻ በአርቃ፣ ቱኒፕ፣ ፫ የሚታኒ ሠፈሮች በቃዴስ ዙሪያ |
ወደ ፫ ቱትሞስ ዘመን መጨረሻ፣ ልጁ 2 አመንሆተፕ የጋራ ፈርዖን በሆነበት ጊዜ (1435 ዓክልበ.) ወደያው ብዙ የሃትሸፕሱት ምስሎችና ካርቱሾች ከቅርሶቿ ለመደምሰስ እንደ ጣረ ይመስላል። አመንሆተፕ የዘመንዋን ትዝታ ከታሪክ ለማጥፋት እንዳሠበ ይመስላል። ከተረፉት ምስሎቿ ብዛት የተነሣ ግን ዘመንዋን ማጥፋቱ ስኬታም እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ቀዳሚው ሃትሸፕሱት |
የግብፅ ፈርዖን 1466-1433 ዓክልበ. |
ተከታይ 2 አመንሆተፕ |