ሃን ዥዎ (ቻይንኛ፦ 寒 捉) በጥንታዊ ቻይና የሥያ ሥርወ መንግሥት ዘመን በዜና መዋዕሎች መሠረት፣ ለጊዜው ከሥያንግ ቀጥሎ መንግሥትን በአመጽ የቀማው ጦር አለቃ ነበር። ይህ ሃን ዥዎ ግን ከቻይና ነገሥታት መካከል አይቆጠረም፤ ዘውዱን ለመጫን አልደፈረም ስለ ነበር ይሆናል።
የቀርከሃ ዜና መዋዕል እንደሚለን፣ በሥያንግ ፰ኛው ዓመት (1967 ዓክልበ. ግ.) ሃን ዥዎ ጀግናውን ሆው ዪን ገደለ፤ ሃን ዥዎም የራሱን ልጅ ጅያውን በጌ ክፍላገር ላይ እንዲዘመት ላከው። በ፳ኛው ዓመት፣ ሃን ዥዎ የጌን ክፍላገር አለቆች አጠፋቸው። በ፳፮ኛው ዓመት፣ ሃን ዥዎ ልጁን ጅያው የሥያንግ መንግሥት ከዠንግጓን ዙሪያ እንዲያጠፋ አደረገ። በሥያንግ ፳፯ኛው ዓመት ጅያው በዠንሡን ዙሪያ ላይ ዘመተ። በወይ ወንዝ ላይ በአንድ ታላቅ ውግያ የዠንሡን ልዑል መርከብ ተገለበጠና ተገደለ። በ፳፰ኛው ዓመት፣ ሃን ዥዎ ልጁን ጅያው ንጉሡን ሥያንግን እንዲገድለው አዘዘ።
የሥያንግ ንግሥት፣ ሚን፣ በዚያን ጊዜ በሥያንግ ልጅ እርጉዝ ነበረች። እርሷ አመለጠችና ወደ አባቷ (የጂንግ ልዑል) አገር በሻንዶንግ ልሳነ ምድር ሸሸች። ሚኒስትሩ ሜ ደግሞ ወደ ዮውጌ ሸሸ። በሚቀጥለው ዓመት ሚን አልጋ ወራሹን ሻውካንግን ወለደች። እርሱ አድጎ ሻውካንግና ቢትዎደዱ ሜ ከ1926 እስከ 1906 ዓክልበ. ድረስ አመጸኖቹን ተዋጉ። በመጨረሻ በ1906 ዓክልበ. በአንዪ በሆነ ውግያ ሃን ዥዎና ልጁ ጅያው ተገደሉ፣ ሻውካንግም ንጉሥ ሆኖ የቻይና መንግሥት ያንጊዜ አልጠፋም።
ቀዳሚው ሥያንግ (ንጉሥ) |
የሥያ (ቻይና) አለቃ (በአመጽ) | ተከታይ ሻውካንግ (ንጉሥ) |