ሆ ቺ ሚን ከ1890-1969 እ.ኤ.አ. የኖረ የቬትናም ኮሚኒስት ፓርቲ መሥራችና መሪ ነበር። ሆ ቺ ሚን ከወጣትነት ጊዜው ጀምሮ ለአብዮታዊ ተግባራት የቆመ ነበር።
ሆ ቺ ሚን በሥራ ምክንያት ፈረንሳይ ውስጥ በነበረበት ወቅት የካፒታሊስት ሥርዓት ምን ያህል ሠርቶአድሩን ሕዝብ ለሥቃይና ለመከራ እንደዳረገውና የዓለም ወዛደሮች በቀለም በቋንቋና በባህል ቢለያዩም ብሶታቸው አንድ መሆኑን በቅርብ ተገነዘበ። በአፍሪካና በእስያ የኢምፔሪያሊስቶች መምጣት ምን ያህል ሥቃይና ውርደት በእነዚህ ሕዝቦች ላይ እንዳደረሰ ተረዳ። በዚህም ምክንያት ሆ ቺ ሚን የቬትናም ሕዝብ ጠላት የፈረንሳይ ኢምፔሪያሊዝም እንጂ የፈረንሳይ መላው ሕዝብ አለመሆኑን ደጋግሞ ገልጿል። ሆ ቺ ሚን በ1917 እ.ኤ.አ. በፈረንሳይ ወዝአደሮች ትግል ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን የፈረንሳይ ሶሻሊስት ፓርቲ አባል ሆነ። ከዚህም በላይ በፈረንሳይ የቬትናም አርበኞችን ማኅበር በማቋቋም በፈረንሳይ ይኖሩ የነበሩትን ቬትናማውያን በማንቃትና በማስተማር ለሀገራቸው ነፃነትና ክብር እንዲታገሉ ያነሣሣ ነበር።
የጥቅምቱ የሩሲያ አብዮት ለአያሌ ዓመታት በዓለም ሰፍኖ የነበረውን የኢምፔሪያሊዝም ብቸኛ የበላይነት ሰባብሮ አዲስ ዘመን በማብሰሩ ሆ ቺ ሚን የጀመረውን ትግል ከግብ ለማድረስ የቦልሼቪኮችን ፈለግ መከተል እንዳለበት አመነ።
በሆ ቺ ሚን አስተሳሰብ የቬትናም ብቻ ሳይሆን የሌሎች ቅኝ ተገዥ የሆኑ ሀገሮች ነፃነት የሚገኘው የወዝአደሩን የአብዮት ጎዳና በመከተል ብቻ እንደሆነ አጥብቆ ያምን ነበር። የነዚህ ሀገሮች ብሔራዊ ነፃነት ከማኅበራዊ ነፃነት ጋር መያያዙንና ይህም ነፃነት ከሶሻሊዝምና ከኮሚኒዝም ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑን አስገንዝቧል።
ሆ ቺ ሚን ከ1924 እስከ 1930 እ.ኤ.አ. በቻይናና በቬትናም በመዘዋወር ለዚህ ውስብስብ ትግል ግንባር ቀደም አመራር ሊሰጥ የሚችለውን ማርክሳዊ ሌኒናዊ ፓርቲ ለማቋቋም ከፍተኛ ትግል አደረገ። በመጀመሪያም የቬትናም አብዮታዊ ወጣቶች ማኅበር የተባለውን በማቋቋም «ወጣት» በተባለው ጋዜጣ ወጣቱን ለትግል ቀሰቀሰ። በዚህ ዓይነት ከብዙ ጥረትና ትግል በኋላም በ1930 እ.ኤ.አ. የኢንዶቻይና ኮሚኒስት ፓርቲን (ኋላ የቬትናም ሠራተኞች ፓርቲ፤ ዛሬ ደግሞ የቬትናም ኮሚኒስት ፓርቲ) መሠረተ።
በ1935 እ.ኤ.አ. ሞስኮ ውስጥ የተካሄደው የኮሚኒስቶች ስብሰባ አንድ ሰፊ ፀረ ኢምፔሪያሊስት የሆነ ዲሞክራሲያዊ ግንባር እንዲቋቋም በወሰነው መሠረት ሆ ቺ ሚን ቬትሚን የተሰኘውን ሰፊ ፀረ ኢምፔሪያሊስት ግንባር በማቋቋም መላውን ሕዝብ በትግሉ ለማሳተፍ ችሏል።
ዲየን ቢየን ፉ በተባለው ታሪካዊ ስፍራ የቬትናም አርበኞች የፈረንሳይን ጦር በማሸነፋቸው ፈረንሳይ በጀኔቩ ስምምነት መሠረት የቬትናምን አንድነት በማወቅ የሰላም ውል ፈረመች። ነገር ግን ከ1955 እ.ኤ.አ. ጀምሮ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በፈረንሳይ እግር በመተካት የደቡቡን ክፍል ለመቁረስ የጦር ሰፈር በመሥራትና በውስጥ አርበኞች በመጠቀም ጦርነት ከፈተ። ነገር ግን አሜሪካ ከግማሽ ሚሊዮን ወታደሮች በላይና በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ቢያፈስም ቬትናምን ሊያሸንፍ አልቻለም።