ሳሙኤል ላንግሆርን ክሌመንስ (እንግሊዘኛ: Samuel Langhorne Clemens) ወይም በብእር ስሙ ማርክ ትዌይን አሜሪካ ካፈራቻቸው ድንቅ ጸሃፍት መካካል የሚመደብ ደራሲ ነው። ትዌይን በኖቬምበር 1835 ዓ.ም. ሚዙሪ በተባለችው የአሜሪካ ግዛት ተወለደ። 18 ዓመት እስኪሞላው ድረስ ከቤተሰቦቹ ጋር የኖረው ሃኒባል በተባለች እና ሚሲሲፒ ላይ በተቆረቆረች ትንሽ ከተማ-አከል ቦታ ነው። አባቱ በ1847 ሲሞት ትዌይን ትምህርቱን በማቋረጥ በማተሚያ ቤት ውስጥ በሰልጣኝነት ተቀጠረ። ይህን ስራውን በ1857 በመተው የእንፋሎት ጀልባ ነጂ በመሆን መስራት ጀመረ። በዚሁ ስራ በቆየባቸው አመታት ነው ኋላ ላይ አድናቆትን ላተረፉለት የስነ-ጽሁፍ ስራዎቹ የሚሆኑትን እውቀቶች ለማሰባሰብ የበቃው። እሱ ራሱም እንዳለው በዚሁ ስራ ላይ ነው "ማንኛውንም በልብ-ወለድ፣ በግለ-ታሪክም ሆነ በታሪክ ላይ ሊገኙ የሚችሉ የሰው ባህርያትን" ሊያጠና የበቃው።
በ1861 እ.ኤ.አ. የአሜሪካ የእርስ-በርስ ጦርነት በመቀስቀሱ ምክንያት ማንኛውም አይነት የመርከብ ላይ ጉዞ ሲስተጓጎል ትዌይንም ስራውን ለመልቀቅ ተገዷል። ከዚህ በኋላም በውትድርና ወዶ-ገብነት፣ በወርቅ ማእድን ፈላጊነት፣ በጋዜጠኝነት ወዘተ ስረቷል።
በ1869 ዓ.ም የመጀመሪያ ዋነኛ ስራው የሆነውን "The Innocents Abroad" ለማሳተም በቃ። ይኽ ድርሰት ክሌመንስ ራሱ በአውሮፓ እና በእየሩሳሌም ባካሄዳቸው ጉብኝቶች ላይ የተመሰረተ ነው። በ1870 ዓ.ም ኦሊቭያ ላንግዶንን በማግባት ኑሮውን ኮኔቲከት በተባለችው ግዛት አድርጓ በዛው ለ17 ዓመታት ኖሯል። በነዚህ 17 ዓመታት ነው አድናቆት ያተረፉለት ስራዎቹን ማለትም "Roughing It"፣ "The Adventures of Tom Sawyer"፣ Life on the Mississippi"፣ እና ከሁኡ የላቀ የተባለለት ድርሰቱን "The Adventures of Huckleberry Finn"ን ያሳተመው።
ትዌይን በ1910 ዓ.ም አርፎ ሬዲንግ፣ ኮኔቲከት ውስጥ በድኑ አርፏል።