ሥያንግ (ቻይንኛ፦ 相) በጥንታዊ ቻይና የሥያ ሥርወ መንግሥት ፭ኛ ንጉሥ ነበር።
የቀርከሃ ዜና መዋዕል በተባለው ጽሑፍ ዘንድ፣ አባቱ ዦንግ ካንግ ካረፈ በኋላ (1974 ዓክልበ. ግድም) ሥያንግ ተከተለው። ዋና ከተማውን ወዲያው ከዠንሡን ወደ ዲጭዩ (አሁን ሻንግጭዩ) አዛወረና በኋይ ወንዝ ዙሪያ በኖሩት አሕዛብ ላይ ዘመተ። በ፫ኛው ዓመት በፈንግና ኋንግ አሕዛብ ላይ ዘመተ። በ፯ኛው ዓመት የዩ አሕዛብ መጥተው ተገዙለት። በ፰ኛው ዓመት የጦር አለቃ ሃን ዥዎ ጀግናውን ሆው ዪን ገደለ፤ ሃን ዥዎም የራሱን ልጅ ጅያውን በጌ ክፍላገር ላይ ላከው። በ፱ኛው ዓመት (1965 ዓክልበ. ግድም) ሥያንግ ቤተ መንግሥቱን ወደ ዠንግጓን (አሁን ሾውጓንግ) አዛወረው። በ፲፭ኛው ዓመት፣ የሻንግ ልዑል ሥያንግሽዕ «ሠረገላዎችንና ፈረሶችን አዘጋጅቶ ወደ ሻንግጭዩ ገባ።» በ፳ኛው ዓመት፣ ሃን ዥዎ የጌን ክፍላገር አለቆች አጠፋቸው። በ፳፮ኛው ዓመት፣ ሃን ዥዎ ልጁን ጅያው የሥያንግ መንግሥት ከዠንግጓን እንዲያጠፋ አደረገ። በ፳፯ኛው ዓመት ጅያው በዠንሡን ላይ ዘመተ። በወይ በአንድ ታላቅ ውግያ የዠንሡን ልዑል መርከብ ተገለበጠና ተገደለ። በ፳፰ኛው ዓመት፣ ሃን ዥዎ ልጁን ጅያው ንጉሡን ሥያንግን እንዲገድለው አደረገ።
የሥያንግ ንግሥት፣ ሚን፣ በዚያን ጊዜ በሥያንግ ልጅ እርጉዝ ነበረች። እርሷ አመለጠችና ወደ አባቷ (የጂንግ ልዑል) አገር በሻንዶንግ ልሳነ ምድር ሸሸች። ሚኒስትሩ ሚ ደግሞ ወደ ዮውጌ ሸሸ። በሚቀጥለው ዓመት ሚን አልጋ ወራሹን ሻውካንግን ወለደች። እርሱ አድጎ ከ1926 እስከ 1906 ድረስ አመጸኖቹን ተዋጉ፣ በመጨረሻ በ1906 ሃን ዥዎን አሸንፎ ሻውካንግ ንጉሥ ሆነ።
ቀዳሚው ዦንግ ካንግ |
የሥያ (ቻይና) ንጉሥ | ተከታይ ሃን ዥዎ (የአመጸ አለቃ) |