ስኳር በተለይ በምግብ የሚገኙ ልዩ ልዩ ጣፋጭ ካርቦሃይድሬት ኣይነቶች ነው።
ዋና ዋና ንጥል ሶከር አይነቶች ፍሩክቶስ እና ግሉኮስ ናቸው። ግሉኮስ ደግሞ «ዴክስትሮስ» ይባላል። እነዚህ ስኳሮች በተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በማር ይገኛሉ።
ዋንኛው ክሌ ሶከር አይነት ሱክሮስ ነው። ይህ የፍሩክቶስና የግሉኮስ ውሑድ ነው። የገበታ ስኳር ባብዛኛው ሱክሮስ ሲሆን ይህ በብዛት ከሸንኮራ ኣገዳ እና ከስኳር ቀይስር ይወሰዳል። ከጭማቂው ሞላሲስን በማስለየት ስኳሩ ይተርፋል። በቡናማ ስኳር ውስጥ ትንሽ ሞላሲስ ቀርቷል።
ሌሎቹ ስኳሮች የተባሉት ጋላክቶስ (ንጥል ሶከር)፣ ላክቶስ እና ማልቶስ (ክሌ ሶከሮች) ናቸው።
ሸንኮራ አገዳ ለኒው ጊኒ ደሴት ኗሪ ሲሆን በጥንት ወደ ሕንድ አገር እንደ ተዛወረ ይመስላል፤ የቻይና ሰዎች ከ700 ዓክልበ. በፊት ስኳር ከሕንድ እንደ ታወቀላቸው ጽፈዋል። ከሸንኮር አገዳው መስፋፋት በፊት ምግብን ለማጣፈጥ በተለይ ማር ይታወቅ ነበር። የግሪክ ጽሐፊዎች ፐዳኒዮስ ዲዮስኮሪዴስ (60 ዓም ግድም) እና ትልቁ ፕሊኒ (70 ዓም ግድም) እንደ ጻፉ፣ ሸንኮራ በሕንድና በአረቢያ የሚበቅል መድኃኒት እጽ መሆኑን ገለጹ። በ350 ዓም አካባቢ ሕንዶች እንዴት ስኳርን ከሸንኮራው ለማውጣት የሚሠራበትን ዘዴ አገኝተዋል። እስልምና ከተነሣ በኋላ (600 ዓም ጀምሮ) አረቦች ሸንኮራውንና የስኳር ማስወጫ ዘዴ በሰፊ አስለመዱት። ከመስቀል ጦርነቶች (1100 ዓም ግድም) በኋላ የስኳር ፍላጎት በአውሮጳም ይታወቅ ጀመር። የስፔን ሰዎች በአሜሪካ ካሪቢያን ደሴቶች እንደ ሠፈሩ (1500 ዓም ያሕል) የሸንኮራገዳ አዝመራ በዚያም ተከሉ። ሸንኮራገዳ በገሞጂዎች በሞቀ አገር ብቻ ስለሚበቅል ስኳሩን ወደ ስሜናዊ አገራት ለማጓጓዝ ትልቅ የንግድ ሥራ ሆነ።
በ1740 ዓም አንድ የጀርመን ሳይንቲስት ሊቅ አንድሬያስ ማርግራፍ ተመሳሳይ ሱክሮስ ከቀይስር ማስገኘት እንደሚቻል አስረዳ። የስኳር ቀይስር ደግሞ በስሜናዊ አገራት ይበቅላል። አሁንም በርካታ የአለም ስኳር ከቀይስሮች ቢመጣም በዚሁ ዘዴ የሚገኘው ስኳር ስለማይበቃ አብዛኛው ስኳር እስከ ዛሬ ከሸንኮራ ይገኛል።
በሳንስክሪት ስኳር «ሸርከራ» ይባል ነበር። ይህ ቃል በቀድሞ ሳንስክሪት «ኮረታኮረት» ማለት ሆኖ ነበር። ይህም በፋርስኛ «ሸከር»፣ በአረብኛ «ሱካር»፣ በአማርኛ «ስኳር»፣ «ሶከር» እና «ሸንኰር» ሆነ። የግሪክኛ «ሳክኻሪስ»፣ ሮማይስጥ «ሱካሩም» እና ሌሎቹ የአውሮፓ ልሳናት እንዲሁም ከዚህ ምንጭ ደረሱ።