ሹቡር

ሹቡር (ሱመርኛ፡ ሱቢር፣ ሱባር፣ ሹባር፣ ሹቡር፤ አካድኛ፦ ሱባርቱ፣ ሹባርቱም፣ ሱባርቱም፣ ሹባሪ) ከሰናዖር ወደ ስሜን በጤግሮስ ወንዝ ላይ የተቀመጠ አገር ነበረ። ይህም ስም በጥንታዊ አማርና ደብዳቤዎችና በኡጋሪት መዝገቦች 'ሽብር' ተጽፎ ተገኝቷል።

ከሁሉ ጥንታዊ በሆነ ዘመን፣ ከሰናዖር (ሱመር) ዙሪያ ሌሎቹ '4 ሩቦች' 'ማርቱ' (አሞራውያን)፣ 'ሱባርቱ'፣ ኤላምና 'ኡሪ -ኪ' (አካድ) ነበሩ። እንዲሁም ኤንመርካርና የአራታ ንጉስ በተባለው ሱመራዊ አፈ ታሪክ፣ ልሣናት የተደባለቁባቸው አገሮች ሹባር፣ ሐማዚ፣ ሱመር፣ ኡሪ-ኪ (የአካድ ዙሪያ) እና የማርቱ አገር ይባላሉ።

ሱባርቱ በአዳብ ንጉስ ሉጋል-አኔ-ሙንዱ መንግሥት ውስጥ አንድ ክፍል ነበረ፤ በኋላ ዘመን የአካድ ንጉስ ታላቁ ሳርጎን በሱባር ላይ አንዳንድ ዘመቻ ያደርግ ነበርና ተከታዩ ናራም-ሲን ከገዛቸው አገራት መካከል ቆጠሩት። የኢሲን ንጉስ ኢሽቢ-ኤራ እና የባቢሎን ንጉስ ሃሙራቢ ደግሞ በሱባር ላይ እንዳሸነፉት ይታመናል።

በአዲሱ የባቢሎን መንግሥት ዘመን በናቦፖላሣር፣ በ2 ናቡከደነጾርና በናቡናኢድ ዘመናት 'ሱባርቱ' ለአሦር በጠቅላላ ዘይቤ ነበር። እንኳን በፋርስ ንጉስ በካምቦሥሥ ዘመን 'ሱባርቱ' የሚለው ስም ይጠቀም ነበር።

ከሊቃውንት ብዙዎች 'ሱባርቱ' ለአሦር ቤት ጥንታዊ ስም እንደ ነበር ይቀበላሉ። ሆኖም ከዚያ አገር ትንሽ ወደ ምሥራቅ፣ ስሜን ወይም ምዕራብ እንደ ነበር የሚሉ ሃሳቦች አሉ። አንዳንድም ጸሐፊ ከሑራውያን ጋር ግኙነት እንደነበራቸው ብሏል።