ሜዳሊያዎች ባለ ክብር
የተወለደው ሰኔ 6 ቀን በ1974 አ.ም በአርሲ ተወለደ.
በሀገር አቋራጭ፣ በጎዳና እና በሜዳ ላይ ያከናወናቸው ውድድሮች እና አንፀባራቂ ድሎቹ በታሪክ ከታዩት ታላላቅ አትሌቶች መካከል እንዲመደብ አድርገውታል።[1]
በረጅም ርቀተ ሩጫ የመጨረሻውን ዙር እንደ አጭር ርቀት ሯጭ ሲሮጥ ያዩት ብዙዎች ፍጥነቱን ሲገልጹ “አቦ ሸማኔ” ይሉታል።
ከርሱ ጋር የሮጠው የኬኒያ አትሌት ክፕሮፕ ደግሞ የቀነኒሳን ፍጥነት ሲገልጽ “ከኃይሌ ጋር ስትሮጥ እስከ መጨረሻው እንደምታሸንፍ ተስፋ አድርገህ ትሮጣለህ፤ ተወዳዳሪህ ቀነኒሳ ሲሆን ግን ገና ከመነሻው ያሸንፍሃል” በማለት ነው።
ከ1 ሺህ 500 ሜትር እስከ ማራቶን በተሳተፈባቸው ውድድሮች ከ17 በላይ ክብረ-ወሰኖችን ሰባብሯል።
በአንድ የኦሊምፒክ ውድድር ሁለት ክብረ-ወሰኖችን የሰበረ ድንቅ ሯጭ ነው።
ሀገር አቋራጭ እና የወጣቶች ሻምፒዮናን ጨምሮ ሀገራችንን ወክሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተወዳደረባቸው ርቀቶች 26 የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሐስ አጠቃላይ 31 ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ አስገኝቷል።
ከረጅም ጉዳት በኋላ በዘንድሮው ዓመት በተካፈለበት የቫሌንሺያ ማራቶን በ4ኛነት ቢያጠናቅቅም የጨረሰበት 2:04:19 ሰዓት ከ40 ዓመት በላይ ዕድሜ ከ2፡05 ሰዓት በታች የጨረሰ የመጀመሪያው አትሌት አድርጎታል።
ይህንኑ ተከትሎ የኬንያ ጋዜጦች ለቀነኒሳ “ዕድሜ የማይገድበው” የሚል ቅፅል ስም ሰጥተውታል።
የተወለደው ሰኔ 6 ቀን 1974 ዓ.ም በአርሲ ዞን ቦቆጂ ከተማ ነው። በትምህርት ቤት እያለ በስፖርት ክፍለ ጊዜ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የተመለከቱት አርቆ አሳቢ መምህሩ ወደ አትሌትክሱ ቢገባ ውጤታማ እንደሚሆን በነገሩት መሠረት ነው ሩጫ የጀመረው።
እንደተባለውም ወደ አትሌትክሱ በገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ውጤቶችን አስመዝግቦ ዓለምን አስደምሟል።
ዓለም አቀፍ ውድድር የጀመረው እ.አ.አ በ2001 ሲሆን፣ በመጀመሪያ ሩጫውም የወጣቶች ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮን የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ አጠናቅቋል። በተመሳሳይ ዓመት 3 ሺህ ሜትር ክብረ-ወሰን የሰበረ ሲሆን፣ ይህ ክብረ-ወሰን ለሦስት ዓመት ተኩል ቆይቷል።
እ.አ.አ 2000 እና 2001 በኔዘርላንድ የተደረጉትን የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በአንደኝነት አጠናቅቋል። በ19 ዓመቱ የጀመረውን ሀገር አቋራጭ ውድድር ለተከታታይ አምስት ዓመታት በአሸናፊነት በማጠናቀቅ 11 የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል።
የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰኖችን እ.አ.አ ከ2004 እስከ 2020 ባሉት ተከታታይ 16 ዓመታት ማንም ሳይሰብራቸው የግሉ አድርጓቸው ቆይቷል።
በ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ ላይ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም በ5 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።
በ2008 የቤጂንግ ኦሊምፒክ ደግሞ በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር ውድድሮች በሁለቱም ውድድሮች ክብረ-ወሰን በመስበር ጭምር የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ ደማቅ ታሪክ ጽፏል።
በዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ታሪክ በ12 ኪሎ ሜትር ስድስት እና በ4 ኪሎ ሜትር ደግሞ አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን፣ በአጠቃላይ 11 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያሸነፈ እጅግ ስኬታማ አትሌት ነው።
እ.አ.አ በ2003፣ 2005፣ 2007 እና 2009 በተካሄዱ አራት ተከታታይ የዓለም ሻምፒዮናዎች በመሳተፍ በ10 ሺህ ሜትር 4 የወርቅ፣ በ5 አንድ የወርቅ እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሸንፏል።
ቀነኒሳ በ2003 በ10 ሺህ ሜትር ዓለም አቀፍ ሩጫ ማድረግ ከጀመረበት እስከ 2011 ድረስ ያልተሸነፈ ብቸኛ አትሌት ነው።
በ2006 በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናም በ3 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ነበረ።
በ2014 የውድድር ዘመን በፓሪስ ማራቶን ድል የተቀዳጀ ሲሆን፣ ያስመዘገበው ሰዓት በታሪክ ስድስተኛውን ፈጣን የማራቶን ውድድር ሰዓት ሆኖ ተመዝገቧል።
እ.አ.አ መስከረም 25 ቀን 2016 የበርሊን ማራቶንን 2:03.03 በሆነ ሰዓት አሸንፏል። በውድድሩ አዲስ የግል ምርጥ ሰዓቱን ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም በውድድሩ ታሪክ ሦስተኛው ፈጣን የማራቶን ሰዓት ነበረ።
ቀነኒሳ ኢንተርናሽናል ውድድሮችን መሳተፍ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 22 ዓመታት ከ168 በላይ ኢንተርናሽናል ውድድሮችን አድርጓል። ይህም በአማካይ ከ7 በላይ ኢንተርናሽናል ውድድሮችን በየዓመቱ አድርጓል ማለት ነው።
5 ሺህ ሜትርን ስድስት ጊዜ ከ12 ደቂቃ ከ48 ሰኮንድ በታች ገብቷል፤ አራት ጊዜ ደግሞ ከ12 ደቂቃ ከ49 ሰኮንድ እስከ 12 ደቂቃ ከ53 ሰኮንድ ውስጥ ገብቶታል።
10 ሺህ ሜትርን ሰባት ጊዜ ከ26 ደቂቃ ከ46 ሰኮንድ በታች፤ ሦስት ጊዜ ደግሞ ከ26 ደቂቃ ከ48 ሰኮንድ እስከ 26 ደቂቃ ከ53 ሰኮንድ ውስጥ አጠናቋል።
የእንግሊዙ ሞ ፋራ የቀነኒሳን አይቶ እሱ የሮጠውን ያህል እሮጠዋለሁ ብሎ አስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ሞክሮ ሲያየው ሊቀርብ ቀርቶ ለመጠጋት ሲያቅተው “ወላሂ እሱ ጨካኝ ነው” ሲል ገልጾታል።
አትሌት ቀነኒሳ በአትሌቲክሱ መድረክ የኢትዮጵያን ስም በማስጠራቱ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተሬት ተሰጥቶታል።
ቀነኒሳ ጉዳት ተደጋግሞበት ለረጅም ጊዜ ከውድድር ባያርቀው በአትሌቲክሱ ዘርፍ ማንም ሊደርስበት የማይችለውን ታሪክ ሊያስመዘግብ ይችል እንደነበረ ብዙዎች ይናገራሉ።