ቄኔዝ (ዕብራይስጥ፦ קְנָז /ቅናዝ/) በብሉይ ኪዳን መሠረት የካሌብ ታናሽ ወንድምና የእስራኤል መስፍን ጎቶንያል አባት ነበር። (መጽሐፈ ኢያሱ 15:17፣ መጽሐፈ መሳፍንት 1:13፣ ፩ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4:13።) ከዚህ በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለዚያው ቄኔዝ ሌላ መረጃ አይሰጠም።
አንድ ሌላ ጥንታዊ የአይሁዶች ታሪክ ከ62 ዓም አስቀድሞ የተጻፈው «የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊነት» (ሮማይስጥ፦ Liber Antiquitatum Biblicarum) ይባላል። በዚህ ታሪክ ዘንድ፣ የእስራኤላውያን መሪ ኢያሱ ወልደ ነዌ ካረፈ በኋላ፣ ይህ ቄኔዝ የካሌብ ልጅ ሲሆን ለመጀመርያው መስፍን በጡሚም ተመረጠ፤ ለ57 ዓመታት እስራኤላውያንን መራቸው። ስለ ቄኔዝ አገዛዝ ታሪክ አንዳንድ ምዕራፍ ይጽፋል።
ከዚህ በኋላ ሌላ ሰው ዜቡል ተሾመባቸው፣ ዜቡልም ለ25 ዓመት መራቸው። ከዚህም በኋላ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሆኑና በሓጾር ንጉሥ ኢያቢስ ስር ለ20 ዓመታት ተገዙ። ስለዚህ፣ ይህ ሰነድ በመጽሐፈ መሳፍንት የተጠቀሱትን የኲሰርሰቴም (8 አመታት)፣ የጎቶንያል (40 ዓመታት)፣ የዔግሎም (18 ዓመታት)፣ እና የናዖድ (80 ዓመታት) ዘመናትን ይዘልላል።
በአንድ የዮሴፉስ ቅጂ ደግሞ ለጎቶንያል ስም በፈንታው «ቄኔዝ» አለው። አንድ ሌላ ሰነድ «የነቢያት ሕይወቶች» (ወይም «ሐሣዊ አጲፋኖስ») እንዳለው፣ ነቢዩ ዮናስ የተቀበረው «በቄኔዝ ዋሻ ውስጥ ሲሆን እሱም በግርግሩ ወቅት የአንዱ ነገድ መስፍን ነበረ።»[1]
በመጽሐፈ መሳፍንት የኲሰርሰቴም ዘመን ኢያሱ ካረፈ በኋላ ባልተወሰነ ጊዜ ሆነ። ስለዚህ ስለ ቄኔዝና ዜቡል ዘመኖች ያለው ትዝታ ትክክል ከሆነ፣ እነዚህ 82 ዓመታት ከኢያሱ በኋላ እና ከኲሰርሰቴም በፊት (1587-1505 ዓክልበ.) መሰካት ነበረባቸው።
«የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊነት» እንደሚለው የቄኔዝ ወንድም ስም የካሌብ ልጅ «ሴናሚያስ» ይባላል። እንዳጋጣሚ በሌሎች ሰነዶች በሶርያ ያምኻድ ከ1587-1575 ዓክልበ. ግድም የገዛው እርካብቱም ከ«ሃቢሩ» አለቃ ከ«ሸሙመ» ጋር ስምምነት አደረገ። በአንዳንድ መምህር ዘንድ ይህ ዕብራውያን በዚያው ወቅት በከነዓን ሃይለኛ እንደ ሆኑ ያሳያል።