ቶቤል፣ ዕብራይስጥ፦ תובל /ቱባል/፣ በኦሪት ዘፍጥረት 10 መሠረት የያፌት ልጅና የኖኅ ልጅ-ልጅ ነበረ። ከዚህ በላይ በትንቢተ ሕዝቅኤል 38፡2-3፣ 39፡1 ቶቤል ይጠቀሳል።
በ1ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም. የአይሁድ ሊቅ ፍላቪዩስ ዮሴፉስ እንዲህ ብሎ ጻፈ፦ «ቶቤል የቶቤላውያን (ጦቤሌስ) አባት ሆነ፤ አሁንም ኢቤራውያን (ኢቤሬስ) ይባላሉ።» ይህ በአናቶሊያና በኋላ በካውካሶስ ተራሮች የተገኘ ሕዝብ ነበር። የካውካሶስ ኢቤራውያን ሕዝብ ከዛሬው ጂዮርጂያ ወላጆች መካከል ነበሩ።
የክርስትና ጳጳሳት አውስታጥዮስ ዘአንጥዮኪያ (330 ዓ.ም. ግድም) እና ቴዎዶሬቶስ (450 ዓ.ም. ግድም) ደግሞ ይህንን ታሪክ ተቀበሉ። ዳሩ ግን ጀሮም (400 ዓ.ም. ግድም)፣ ኢሲዶር (635 ዓ.ም. ግድም) እና ነኒዩስ (830 ዓ.ም. ግድም) እንዳሉት፣ የቶቤል ተወላጆች ኢቤራውያን ብቻ ከመሆናቸው በላይ፣ ጣልያውያን (የጥንት ጣልያን ኗሪዎች) እና እስፓንያውያን ከቶቤል ተወለዱ። (የድሮ እስፓንያ ሰዎች ደግሞ «ኢቤራውያን» ተባሉ።) ቅዱስ አቡሊድስ ሌላ ልማድ ዘገበ፤ የቶቤል ዘሮች «ሄታሊ» (ወይም በአንዳንድ ቅጂ ተሰላውያን) እንደ ሆኑ ጻፉ። የሱርስጥ ጽሑፍ መጽሐፈ ንብ (1214 ዓ.ም. ግድም) ቶቤል የቢታንያ ሰዎች አባት እንደ ነበር ይላል።
የኬጥያውያን መንግሥት ከወደቀ በኋላ (1190 ዓክልበ. ግድም) በአናቶሊያ ታባል የተባለ መንግሥት ተገኘ፤ ከቶቤል ልጆች እንደ ወጣ የሚያምኑ አሉ። እንዲሁም ጎረቤቶቻቸው ሙሽካውያን ከሞሳሕ እንደ ወጡ ይታመናል። ከዚህም ዘመን በኋላ ግሪኮች ቲባሬኒ የሚባል ሕዝብ በአናቶሊያ ያውቁ ነበር።
በአንድ ካታሎኒያ (ምሥራቅ እስፓንያ) ተውፊት ዘንድ፣ የያፌት ልጅ ቶቤል ከኢዮጴ (አሁን ተል አቪቭ) ከቤተሠቡ ጋር በመርከብ ወደ እስፓንያ ፍራንኮሊ ወንዝ ከባቢሎን ግንብ ውድቀት በኋላ 12 ዓመት ደረሰ፤ በዚያም ስለ ልጁ «ታራሆ» ስም ከተማ መሠረተ (የአሁን ታራጎና)። ከዚያ ወደ ኤብሮ ወንዝ ወጣ፤ ይህም የሁለተኛው ልጅ «ኢቤር» ስም አለው፣ አምፖስታን እዚያ ሠራ። የሦስተኛው ልጁ ስም «ሰምፕቶፋይል» ይባላል። ኖህ (ወይም የኖህ 4ኛው ልጅ ያኑስ) ከመቶ አመት በኋላ እዚህ እንደ ጎበኛቸው ይጨምራል። በዚህ ተውፊት፣ ቶቤል ለ155 አመት በእስፓንያ ነገሠ፣ ወደ ማውሬታኒያም (አሁን ሞሮኮ) ለመስፋፋት ሲል ሞተና ልጁ ኢቤር ተከተለው። ከዚህ በላይ ራቬና በጣልያ፣ ሴቱባል በፖርቱጋል፣ ቶሌዶ እና ብዙ ሌሎች ከተሞች በእስፓንያ[1] ሁላቸው በቶቤል ያፌት እንደ ተመሠረቱ የሚሉ ልማዶች አሉ። በተጨማሪ፣ የቶቤል ሚስት ስም «ኖያ» እንደ ነበር፣ በሳን ቪንሴንቴ ርእሰ ምድር ፖርቱጋል እንደ ተቀበረ፣ ወይም በመሞቱ 65፣000 ተወላጆች እንደ ነበሩት የሚሉ ልማዶች አሉ። ንጉስ ቶቤል ሕግጋቱን በከላውዴዎን ቋንቋ አወጣ፤ የ1ዱ አመት ልክ በ365 ቀኖች እና 6 ሰዓቶች አደረገው፤ የቤትንም አሠራር፣ እህልንም ወደ ዳቦ መጋገር፣ ወዘተርፈ ኑሮ ዘዴ ለሕዝቡ እንዳስተማረ ይባላል።[2]
የነዚህ ትውፊቶች ምንጭ አኒዮ ዳ ቪቴርቦ በ1490 ዓ.ም. ያሳተመው ሀሣዊ ቤሮሦስ የተባለው ሰነድ ይመስላል፤ ይህ ጽሑፍ ግን ባብዛናው እንደ እውነተኛ ታሪክ አይቆጠረም። ነገር ግን ከዚያ በፊት በአራጎን መምህር-ንጉስ 4 ፔድሮ (1360 ዓ.ም. ግድም) መሠረት ቶቤል መጀመርያ በእስፓንያ የሰፈረ ሰው ነበር፣ ጀሮምና ኢሲዶርም እንደ ጻፉ እቤራውያን ከርሱ ተወለዱ፣ በቀድሞ «ሴቱባሌስ» ተብለው በኤብሮ ወንዝ ሠፈሩ፣ በኋላም ስለዚያ ወንዝ ስማቸውን ወደ «ኢቤራውያን» ቀየሩ። እንዲሁም በ1270 ዓ.ም. ግድም የጻፉት የካስቲል መምህር-ንጉሥ 10 አልፎንሶ ተመሳሳይ አፈ ታሪክ አቀረቡ፤ በርሳቸው ጽሁፍ ግን ቶቤል በፒሬኔስ ተራሮች ውስጥ በአስፓ ተራራ ሠፈረ፤ «ሴቱባሌስ» የሚል ስም መጀመርያ ክፍል ከ«ሴቱስ» መጥቶ ትርጉሙ ነገድ ማለት መሆኑን ጨመሩ። በሳቸው ዘንድ ስማቸው በኋላ «ሴልቲቤራውያን» (ቄልቲቤራውያን) ሆነ።
ከዚህም በፊት በ740 ዓ.ም. ያህል የጻፈው ታሪክ ጸሐፊ አቡልቃሲም ታሪፍ አበንታሪክ እንዳለው፣ የያፌት ልጅ ቶቤል (ወይም «ሴም ቶፋይል») እስፓንያን በ3 ልጆቹ መካከል አካፈለው፤ በኲሩ ታራሆ ወደ ስሜን-ምሥራቅ ያለውን ክፍል (ታራሆን፣ በኋላ አራጎን) ተቀበለው። ሁለተኛው ልጅ፣ ዳግማዊ ሴም ቶፋይል፣ በምዕራብ በውቅያኖስ አጠገብ ያለውን ክፍል (ሴቱባል) ወረሰ፤ ታናሹም ኢቤር በምሥራቅ በሜድትራኔአን አጠገብ ያለውን ክፍል (ኢቤሪያ) ተቀበለ። ከዚያ ቶቤል ለራሱ «ሞራር» የተባለ ከተማ ሠራ፣ ይህም አሁን ሜሪዳ፣ እስፓንያ ነው። አበንታሪክ ይህን ዝርዝር ከከተማው ዋና መግቢያ በር በላይ ከተገኘው ድንጊያ ተቀርጾ እንዳነበበው ወደ አረብኛም እንዳስተረጎመው ይለናል።
በስሜን እስፓንያ በሚገኘው ባስክ ብሔር በኩል ደግሞ የባስክ ሊቅ ፖዛ (15ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም.) የጻፈው ቶቤል የባስኮች (የኢቤራውያንም) አባት እንደ ነበር ነው። የፈረንሳይ ባስክ ጸሐፊ ኦጉስተን ቻሆ (19ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም.) «የአይቶር ተውፊት» አሳተመ፤ የባስኮች አባት አይቶር ከቶቤል ዘር እንደ ነበር ይላል።
ቀዳሚው የለም (አዲስ መንግሥት) |
የቱባሊያ (ኢቤሪያ) ንጉሥ | ተከታይ ኢቤሩስ |
በአይሁድ ረቢዎች ምንጮች የቶቤል ልጆች ስሞች ይለያያሉ። በሀሣዊ ፊሎ (62 ዓ.ም. ግድም) ልጆቹ «ፓናቶባ» እና «ኤቴባ» ሲሆኑ፣ «ፔዔድ» የሚባል አገር ለርስታቸው ተሰጡ። በመካከለኛ ዘመን የታየው የይራሕሜል ዜና መዋዕል ልጆቹን «ፋንቶንያ» እና «አቲፓ» አገራቸውም «ፓሃጥ» ይላቸዋል። በሌላ ሥፍራ ይህ መጽሐፍ ከጀሮም የመጣ መረጃ አለው፤ የቶቤል ልጆች በኢቤርያና እስፓንያ ሠፈሩ ይላል። በሌላ ሥፍራ እንደገና ከዮሲፖን (950 ዓ.ም. ግድም) የወረደ ትውፊት አል። በዚህ ትውፊት የቶቤል ልጆች በቶስካና (የጣልያን ክፍል) ሠፈሩ፤ «ሳቢኖ» የተባለ ከተማ ሠሩ። የኪቲም (ያዋን) ልጆች ግን በዚህ አጠገብ በካምፓንያ ክፍላገር ከተማቸውን «ፖሶማንጋ» ሠሩ። ቲቤር ወንዝ በመካከላቸው ጠረፋቸው ሆነ። ኪቲሞች ግን የሳቢኖ ሴቶች በግድ ከያዙ በኋላ ወደ ጦርነት ሔዱ። ኪቲሞች ለቶቤል ልጆች የጋራ ክልሶቻቸውን ባሳያቸው ጊዜ ጦርነቱ ተጨረሰ። ይህም ትውፊት በአጭሩ በሠፈር ሀያሻር ይገኛል፤ በዚያም የቶቤል ልጆች «አሪፒ»፣ «ኬሴድ»ና «ታዓሪ» ይባላሉ።
የአረብኛ መዝገበ ቃላት «ታጅ አል-አሩስ» (በአል-ዙባይዲ፣ 1782 ዓ.ም.) እንደ ዘገበው፣ አንዳንድ የእስላም ደራሲ ካዛሮች (በአሁኑ ሩስያ የኖሩ) ከሞሳሕ እንደ ተወለዱ ሲያምኑ፣ ሌሎች ግን ካዛሮችና ስላቮች ከወንድሙ ቶቤል እንደ ተወለዱ ይላሉ።[3]
|