ኤንሊል-ባኒ በሱመር የኢሲን ሥርወ መንግሥት ፲ኛው ንጉሥ ነበረ (1772-1749 ዓክልበ. የነገሠ)። የኤራ-ኢሚቲ ተከታይ ነበረ።
«የቀድሞ ነገሥታት ዜና መዋዕል» የሚባለው ጽላት ስለ ኤንሊል-ባኒ እንዲህ ይላል፦
- «ንጉሡ ኤራ-ኢሚቲ የአጸድ ጠባቂውን ኤንሊል-ባኒን እንደ (ጊዜያዊ) ምትኩ ሾመው፤ ንጉሣዊ ዘውዱንም በራሱ ላይ አጫነው። ኤራ-ኢሚቲ ትኩስ ሾርባ እየዋጠ እቤተ መንግሥት ሞተ። በዙፋኑ የተቀመጠው ኤንሊል-ባኒ አልተወውም፤ ለንጉሥነቱ ተሾመና።»[1]
በሱመራዊ ነገሥታት ዝርዝር ላይ ፳፬ ዓመታት እንደ ነገሠ ሲለን፣ ፲፮ ዓመት ስሞች ያህል ይታወቃሉ።[2] ከነዚህ መካከል፦
- 1 - «ኤንሊል-ባኒ ንጉሥ የሆነበት ዓመት» (1772 ዓክልበ. ግ.)
- a - «ንጉሥ ኤንሊል-ባኒ የኢሲን ዜጎች ከግብር ነጻ ያወጣቸውበት ዓመት»
- c - «ንጉሥ ኤንሊል-ባኒ፣ የሱመርና የአካድ ንጉሥ፣ ኒፑርን ወደሚገባው ሥፍራ የመለሰበት ዓመት»
ብዙ ሌሎች ዓመታት የወርቅ ጣኦታት ስለማሥራታቸው ተሰየሙ።
የኤንሊል-ባኒ ጽላት እንዲህ ይላል፦
- « በኒፑር ፍትሕ መሠረትኩ፣ ጽድቅም አስፋፋሁ። እንደ በጎች መኖ ፈለግኩላቸው፣ በትኩስ ሣር መገብኳቸው። ከባድ ቀንበር ከአንገታቸው አነሣሁና በጽኑ ቦታ አኖርኳቸው። ፍትሕ በኒፑር መሠርቼ ልባቸውንም ጸት አድርጌ፣ ፍትሕና ጽድቅ በኢሲን መሠረትኩና የሀገሩን ልብ ጸት አደረግኩ። የገብስ ግብር ከ 1/5 (20%) እስከ 1/10 (10%) ድረስ ቀነስኩ። ሙሽኬኑም (አገልጋይ መደብ) ከወሩ አራት ቀን ብቻ አገለገለ። የቤተ መንግሥት ከብት በሕዝብ እርሻዎች ሲሰማሩ ሕዝቡም «ሻማሽ (አምላክ) ሆይ» ብለው አቤቱታ ሲያሰሙ፣ እኔ የቤተ መንግሥትን ከብት ከዚያ ሕዝብ እርሻዎች አባረርኋቸው፣ ሕዝቡም «ሻማሽ ሆይ» የሚሉትን አቤቱታ ተሰናበትኩ።»
በአስናፈር (677-638 ዓክልበ. የአሦር ንጉሥ) መጻሕፍት ቤት አንድ ሕክምናዊ ሰነድ «የሰው አዕምሮ እሳት ሲኖረው» ተገኝቶ ኤንሊል-ባኒን ይጠቅሳል። «ፍቱንና ተግባራዊ ቅባቶችና ልቊጦች፣ ከማየ አይኅ አስቀድሞ በሹሩፓክ በኖሩት ሊቃውንት ዘንድ፤ የኒፑር ሊቅ ኤንሊል-ሙባሊት በኤንሊል-ባኒ ፪ኛ ዓመት ዘገበው።»
የኤንሊል-ባኒ ተከታይ ዛምቢያ ነበር፤ የዛምቢያ አባት ስም አይታወቅም።
- ^ "ABC20". Archived from the original on 2006-02-28. በ2014-06-11 የተወሰደ.
- ^ የኤንሊል-ባኒ ዓመት ስሞች