ክሬዲት ካርድ ሸቀጦችንና አገልግሎትን ለመግዛት የሚያስችል የፕላስቲክ ካርድ ነው። ክሬዲት ካርድ ከሌሎች የመክፈያ ስርዓቶች ይለያል። ለምሳሌ ዴቢት ካርድ አሁን-ግዛ አሁን-ክፈል ስርዓት ሲሆን፣ ክሬዲት ካርድ በአንጻሩ አሁን-ግዛ፣ ቆይተህ-ከፍል ስርዓት ነው። ሌላው ልዩነት፣ ቼኪንግ አካውንት እና ሴቪንግ አካውንት የራስ የተጠራቀመ ገንዘብን ሲጠቀሙ፣ ክሬዲት ካርድ በአንጻሩ የአራጣ አይነት ነው። ክሬዲት ካርድ ከቻርጅ ካርድ እንዲሁ ይለያል። የቻርጅ ካርድ ዕዳ በየወሩ በሙሉ መከፈል ሲኖርበት የክሬዲት ካርድ ዕዳ ግን የግዴታ በሙሉ መከፈል የለበትም፤ ነገር ግን በሙሉ ካልተከፈለ በዕዳው ላይ ወለድ ይጨመርበታል።
ክሬዲት ካርድ የሚሰጡ ባንኮችና ሌሎች ተቋማት ክሬዲት ከመስጠታቸው በፊት የደንበኞችን የክሬዲት ታሪክ ይመረምራሉ። በተጨማሪይ የደንበኛቸውን የአሁን አቅም፣ ገቢና ወጭ ይመረምራሉ። ቋሚ ገቢና ብዙ ወጭ የሌለባት ደንበኛ በክሬዲት ተቋማት ዘንድ ብዙ ተቀባይነት ይኖራታል ማለት ነው። በዚህ መልክ ለክሬዲት የተፈቀደች ደንበኛ፣ ውሱን የወጪ መጠን በካርዷ ላይ ተደርጎ ክሬዲት ይፈቀድላታል።
ክሬዲት ካርድን በአቅም ልክ መጠቀም ጥሩ ነው። ለማናቸውም አይነት ክፍያዎች በክሬዲት መክፈል ይቻላል። በተለይ ለድንገተኛ ወጪ፣ ክሬዲት ጥሩ ነው። ሆኖም ወጪን በየወሩ መክፈል ግድ ይላል። ለዚህ ተግባር የዳይሬክት ዴቢት አካውንት ማቋቋም ጥሩ ነው።
በአጠቃላይ መልኩ፣ በክሬዲት የተከፈለን ወጪ በየወሩ በሚላክ የክሬዲት ቢል አማካይነት መክፈል ደንበኞች ዕዳ ውስጥ እንዳይገቡ ይረዳል። ክሬዲት ሰጪ ተቋማት በየወሩ በሚልኩት ቢል ላይ የሚያስቀምጡት አንስተኛ ክፍያ አለ። ይህ ክፍያ ለወጭ ከተከፈለው ገንዘብ ያንሳል። ይህን አንስተኛ ክፍያ መክፍል ይቻላል፣ ሆኖም አበዳሪ ተቋማት ባልተከፈለው እዳ ላይ ከፍተኛ ወለድ ይጭናሉ። የወለዱ መጠን በአበዳሪው ተቋም ፍላጎት ሊቀየር ይችላል፤ ስለሆነም በተቻለ መጠን የየወሩን ዕዳ መክፈል በጣም ጠቃሚ ነው።
ምሳሌ፡ አንድ ሰው 200 ብር በክሬዲት ቢከፍል። የክሬዲት ካርዱ ወለድ 21% ቢሆንና በየወሩ የተፈቀደውን አንስተኛ ክፍያ 10 ብር ቢከፍል፣ የሚደርስበት ጥቅምና ጉዳት ምንድን ነው?
ከጥቅም አንጻር፣ 200 ብሩን ወዲያው መክፈል የለበትም፣ ስለሆነም በጊዜው 200 ብር ባይኖረውም ዕቃውን ለመግዛት ክሬዲቱ አስችሎታል። ከጉዳት አንጻር፣ በየወሩ የሚጠራቀመውን ወለድ እና የመጀመሪያ ብድሩን ከፍሎ ለመጨረስ 25 ወራት ይወስድበታል። በኒህ ወራት፣ ከተበደረው ውጭ 48 ብር ተጨማሪ እዳ ይከፍላል።
አንድ ሰው ካለው የመግዛት አቅም እኩል በክሬዲት ከከፈለ፣ ያ ሰው ምንጊዜም የክሬዲቱን ወለድ በመክፈል የመጀመሪያው ዕዳ እንዳለ ይኖራል።