ኲሰርሰቴም

ኲሰርሰቴም (ግሪክኛ፦ Χουσαρσαθαίμ /ኹሳርሳጣይም/፣ ዕብራይስጥ፦ כושן רשעתים /ኩሻን ሪሽዓተይም/) በብሉይ ኪዳን መጽሐፈ መሣፍንት 3:1-11 መሠረት ዕብራውያንን ለ8 ዓመት የገዛ የመስጴጦምያ (ዕብ.፦ አራም-ናሓራይም) ንጉሥ ነበር።

በዚያ እንደሚዘገብ፣ ከኢያሱ ወልደ ነዌ መሪነት ካልተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ዙሪያ የቀሩት ሕዝቦች፦ ፍልስጥኤማውያንሲዶናውያን (ፊንቄ) እና ሌሎች የተረፉት የከነዓን አሕዛብ ፡ ይፈተኑዋቸው ነበር። ከኬጥያውያንአሞራውያንና ከነዓናውያን ጋር ተጋብተው ወደ ጣኦታቸውም (በአሊምና አስታሮት) ይዞሩ ጀመር። እግዚአብሔርም ዕጅግ ተቆጥቶ ወደ ኲሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው ይላል። ለስምንት አመት ከተገዙለት በኋላ፣ ለእግዜር ስለ ጮኹ እርሱ የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያልን እንደ መሪ አስነሣላቸው። ጎቶንያልም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ የእስራኤል ልጆች ንጉሥ ኲሰርሰቴምን ድል ለማድረግ ቻሉና ጎቶንያል ከዚያ ለአርባ ዓመት በሰላም መራቸው።

ፕሲውዶ-ፊሎ የተባለው ጥንታዊ አይሁድ ታሪክ መጽሐፍ እንዳለው፣ የጎቶንያል አባት ቄኔዝና ሌላ ሰው ዜቡል ለ82 ዓመት ከኢያሱ ቀጥሎ ፈራጆች ሆኑ ይላል፤ ከዚያ ታሪኩ ወደ ዲቦራ ዘመን ይዘልላል እንጂ ኲሰርሰቴምን አይጠቅሰውም። ከንጉሥ ሳኦል በፊት የተዘረዘሩት ዓመቶች በመጽሐፈ መሣፍንት ተሰጥተው ኲሰርሰቴም የገዙባቸው ስምንት ዓመታት ከ1505-1497 ገደማ ከክርስቶስ በፊት እንደ ነበሩ ይመስላል።

የንጉሡ ስም በዕብራይስጡ «ኩሻን-ሪሽዓተይም» ትክክለኛ እንደሚሆን አይታስብም። ምክንያቱም «ሪሽዓተይም» የሚለው ዕብራይስጥ ቃል ሲተረጎም «ኹለት ክፋቶች» ለማለት ነው። መጠሪያው በስድብ እንደ ተለወጠ ይታስባል። እንዲሁም ሀገሩ በዕብራይስጡ «አራም-ናሓራይም» ሲባል ይህ ማለት የካራን ዙሪያ ወይም ስሜኑ መስጴጦምያ ነው፤ የ«ናሓራይም»ም ወይም እንደ አረማይክ «ናሓራይን» ትርጉም «ኹለት ወንዞች» ነው። በዚሁም ወቅት ያሕል (1512 ወይም 1508 ዓክልበ. ያሕል) «ናሕሪን» ወይም ሚታኒ የተባለ መንግሥት እዚያ በንጉሥ ኪርታ እንደ ተመሠረተ ይታመናል። «የከረት ትውፊት» የተባለው ኡጋሪትኛ ድርሰት እንደሚገልጽ፣ ይህ ንጉሥ ከረት ወይም ኪርታ (ክ-ር-ት) በሶርያ ሑራውያን ብቻ ሳይሆን በከነዓንና በሐቢሩ ወዘተ. ላይ ያንጊዜ እንደ ገዛ በቀላል ይቻላል።