ዐግ

እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት የያዙት ግዛቶች ሐሴቦንና ባሳን፣ በኋላ ገለዓድ

ዐግ (ዕብራይስጥ עוֹג /ዖግ/) በብሉይ ኪዳን ዘንድ እስራኤላውያንሙሴ መሪነት በኤድራይ ውጊያ እስካሸነፉት ድረስ (ምናልባት 1621 ዓክልበ.) የባሳን አገር (በአሁን ዮርዳኖስ) አሞራዊ ንጉሥ ነበር።

መጀመርያ ሲጠቀስ ኦሪት ዘኊልቊ እንደሚገልጽ፣ ይህ ውግያ ሌላውን አሞራዊ የሐሴቦን ንጉስ ሴዎንን ካሸነፉት ቀጥሎ ሆነ።

«ተመልሰውም በባሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ ይወጋቸው ዘንድ ወጣ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲህ ታደርግበታለህ አለው። እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ መቱ ሰውም አልቀረለትም፤ ምድሩንም ወረሱ።» ኦሪት ዘኊልቊ 21:33-35

ተመሳሳይ ዐረፍተ ነገሮች እንደገና በኦሪት ዘዳግም 3:1-3 ይደገማሉ፣ ከዚያም እንዲህ ይቀጠላል፦

«በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን፣ አንድም ያልወሰድነው የለም፤ በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት፥ የአርጎብን አገር ሁሉ፥ ስድሳ ከተሞችን ወሰድን። በቅጥር ካልተመሸጉት ከእጅግ ብዙ ከተሞች ሌላ፥ እነዚህ ከተሞች ሁሉ ቁመቱ ረጅም በሆነ ቅጥር በመዝጊያና በመወርወሪያም የተመሸጉ ነበሩ። ...
«በዚያም ዘመን ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ አርሞንኤም ተራራ ድረስ ምድሪቱን በዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩት ከሁለቱ ከአሞራውያን ነገሥታት እጅ ወሰድን... በሜዳውም ያሉትን ከተሞች ሁሉ፥ ገለዓድንም ሁሉ፥ በባሳንም ያሉትን የዐግን መንግሥት ከተሞች እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ድረስ ባሳንን ሁሉ ወሰድን። ከራፋይም ወገን የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻውን ቀርቶ ነበር፤ እነሆ፥ አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፤ እርሱ በአሞን ልጆች አገር በረባት አለ፤ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ በሰው ክንድ ልክ ነበረ። »
የዐግ አልጋ (ዘዳግም 3:11) በ1762 ዓም እንደ ተሳለ

«ራፋይም» ደግሞ በኦሪት ዘንድ በሎጥ ዘመን ከዮርዳኖስ ምሥራቅ የተገኘ ወገን ሲሆን (ዘፍጥረት 14:5)፣ በሗላ ከሎጥ የተወለዱት ብሔሮች አሞናውያንና ሞአብ አገራቸውን ያዙ (ዘዳግም 2:9, 19, 22)። ሞአባውያን እነዚህን ሰዎች «ኤሚም» ሲሉዋቸው (ዘዳግም 2:10)፣ አሞናውያንም «ዘምዙማውያን» (ዘዳግም 2:20) ይሉዋቸው ነበር። እንዳጋጣሚ ዕብራይስጡ ስማቸው «ራፋይም» በሌላ ሥፍራ «የሙታን ጥላዎች» ይተረጎማል፤ የብሔሩም ትክክለኛ ስም «የዔናቅ ልጆች» እንደ ሆነ፣ «በቁመት የረዘሙ» እንደ ሆኑ በዘዳግም 2:10-11 ይገለጻል። የዔናቅም ልጆች በዘኊልቊ 13:33 «የኔፊሊም ወገን» ይባላሉ። ሆኖም በዘፍጥረት 6:4 «ኔፊሊም» በማየ አይኅ የጠፋ ወገን መሆኑ ግልጽ ስለ ሆነ ሐረጋቸው ከነዚህ ቅድመኞቹ «ኔፊሊም» ሊሆን አይቻልም።

ቢሆንም፣ በሗለኞቹ አይሁድእስልምና ትውፊቶች ዘንድ፣ ይሄ ንጉሥ ዐግ «ከራፋይም ወገን» ሲሆን የኖህ መርከብን በመያዝ ከጥፋቱ ውሃ ለማምለጥ የቻለ በጣም ረጅም ሰው ነበረ። ነገር ግን ይህ በተልሙድ የተመዘገበ ትውፊት የዐግ እድሜ በመገደሉ ከአንድ ሺህ አመታት በላይ ያድርገው ስለ ሆነ ከተለመደው ዜና መዋዕል ጋር ልክ አይሆንም። በሃዲስና በሌሎች እስላማዊ ጽሑፎች ስሙ «ዑጅ ኢብን ዓናቅ» ሲባል እናቱ ደግሞ «ዓናቅ ቢንት አዳም»፣ የአዳም ልጅና የቃየል ክፉ እኅት፣ ተባለች። ስለ «ኡንጁ ቢን ኡኑቅ የሆኑ ተጨማሪ ትውፊቶች በታንዛኒያ ተገኝተዋል፣ ቁመቱም አንድ ማይል እንደ ረዘመ ይላሉ።

በአይሁዶች ባቢሎን ተልሙድ ዘንድ ዐግና ሴዎን ሁለቱ የኦሕያስ ወይም ኦጊያስ ልጆች፣ ኦሕያስም የሰምያዛ (የትጉሃን አለቃ በመጽሐፈ ሄኖክ) ልጅ እንደ ነበር ይላል። በቁምራን የተገኘው «የረጃጅሞች መጽሐፍ» ደግሞ ዘንዶ የገደለውን ኦሕያስንና ሰምያዛን ጠቅሶዋል፣ ያውም ጽሑፍ በኋላ ለማኒኪስም እምነት ይታወቅ ነበር። ዳሩ ግን ከነዚህ ትውፊቶች ውጭ በትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅደም-ተከተል በኖኅ መርከብ ካሉት ስምንት ሰዎች ብቻ በስተቀር አንዳችም ሰው ዘርን እንዳላተረፈ ግልጽ ነው። ስለዚህ በ1621 ዓክልበ. ገደማ የተገደለው የባሳን ንጉሥ ዐግ ከአሞራዊ (ከነዓን) ወገን ነበር የሚለው መረጃ ትክክል ይመስላል።

የዐግ ታላቅ አልጋ በረባት በአሞን አገር ተገኘ ሲል ይህ ከተማ ዘመናዊ አማን፣ ዮርዳኖስ ነው፤ በዚያም ለዚሁ ትልቅ መጠን የሆነ የድንጋዮች ቅርጽ ለሥነ ቅርስ ይታወቃል።