የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩ እና የሚጻፉ ቋንቋዎችን፣ እና የምልክት ቋንቋን ያጠቃልላል። በአገሩ ውስጥ ፺ የሚሆኑ ቋንቋዎች አሉ።[1] በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚነገሩት ቋንቋዎች አማርኛ እና ኦሮምኛ ሲሆኑ፤ አማርኛ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ነዋሪዎች የመማሪያ፤ የመገበያያ እንዲሁም የስራ ቋንቋ ሆኖ የቆየ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የስራ ቋንቋ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩት ቋንቋዎች አፍሮ-ኤስያዊ እና ናይሎ ሳህራዊ በሚባሉ ሁለት ዋና የቋንቋ ክፍሎች ሊካተቱ ይችላሉ። በአፍሮ-ኤስያዊ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥም ኩሻዊ፣ ኦሞአዊ እና ሴማዊ የሚባሉ ንዑስ ክፍሎች አሉ።