የኮምፒዩተር አውታር (ኔትወርክ) ማለት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ኮምፒዩተሮችን ማገናኘት ነው። እነዚህ ኮምፒዩተሮች ሲገናኙ መረጃ መለዋወጥ ይቻላል። አውታሩ ውስጥ ያሉት ኮምፒዩተሮች በአንደ ክፍል ውስጥ ወይም በጣም በተራራቁ ሕንጻዎች ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ። ኮምፒዩተሮቹ በኤሌትሪክ ገመድ ፣ በገመድ የለሽ ግንኙነት ወይም በሞደም ሊገናኙ ይችላሉ። አውታሩ ላይ ሌሎች የኮምፒዩተር መሣሪያዎችንም መግጠም ይቻላል። ለምሳሌ አንድ ፕሪንተር አውታር ውስጥ አገናኝቶ አውታሩ ውስጥ ከሚገኝ ማንኘውም ኮምፒዩተር ወደዛ ፕሪንተር ማተም ይቻላል።
የአውታሩን ኮምፒዩተሮች ሁሉንም እኩል ሥልጣን መስጠት ይቻላል ወይም ለአንዳንድ ኮምፒዩተሮች የተለዩ ሥራዎች መሥራት እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል። ሁለተኛው ዘዴ ክላየንት-ሰርቨር ይባላል። አብዛኛው ጊዜ ሰርቨሮቹ ሀይለኛና ትልቅ ሲሆኑ ክላየንቶቹ ደግሞ አነስተኛ ናቸው።