ያው (ቻይንኛ፦ 尧) በቻይና አፈ ታሪክ የጥንታዊ ቻይና (ኋሥያ) ንጉሥ ነበር።
የቀርከሃ ዜና መዋዕል በተባለው ጽሑፍ ዘንድ፣ ያው በአባቱ በዲ ኩ ዘመን «የታንግ ልዑል» የሚለው ማዕረግ ነበረው። ወንድሙ ዲ ዥዕ መጥፎ አድርጎ ለ9 ዓመት ከነገሠ በኋላ በ2133 ዓክልበ. ከዙፋኑ ተጣለና መንግሥቱ ወደ ያው ዞረ። ንጉሥ ያው እጅግ ጥበበኛ ሆኖ ወዲያው በመጀመርያው ዓመት የዘመን መቆጠሪያና የከዋክብት መቆጠሪያ ቁጠራ አዘዘ። በ12ኛው አመት (2122 ዓክልበ.) ቋሚ ሠራዊት በኋሥያ መሠረተ። በ15ኛው አመት (2119 ዓክልበ.) የጁሶ አውራጃ አለቃ ለኋሥያ ግዛት ተገዥ ሆነ። በ19ኛው አመት (2115 ዓክልበ.) የሥራዎች ሚኒስትር ሾመ። በ42ኛው አመት (2092 ዓክልበ.) ብሩህ ኮከብ ታየ። በ58ኛው አመት (2076 ዓክልበ.) ልጁን ዳንዡ ወደ ዳንሽዌ አባረረው። በ61ኛው አመት ከመኳንንቱ ጉን የተባለውን ሚኒስትር ሹሞት፣ ሆ ወንዝ በጎርፍ ምክንያት ሞልቶ ስለፈሰሰ እንዲያስተዳድረው አዘዘው። በ70ኛው አመት በ2064 ዓክልበ. ጉን ስላልቻለውም ሽሮት አዲስ ሚኒስትሩን ሹን እንደ ተከታይ ሰየመው፤ ከሴት ልጆቹም ሁለት ለሹን አጋባቸው። በ73ኛው አመት (2061 ዓክልበ.) ያው የኋሥያን ዙፋን ትቶ ለተከታዩ ለሹን ሰጠው።
ከነገሠ በኋላ በሹን ዘመን ሌላ 28 ዓመታት እንደ ኖረ ይላል። ያው ከሞተ በኋላ በአገሩ ልቅሶ ምክንያት ለ3 አመት ዘፈን እንዳልተሰማ ሲማ ጭየን በጻፈው ሽጂ ይጨመራል።
በሌሎች መዝገቦች ዘንድ፣ ንጉሥ ያው ልጁን ዳንዡ ለማስደሰት «ወይጪ» (ወይም «ጎ») የተባለውን ጨዋታ የፈጠረው ነበር። ዳንዡ ግን እንደ አባቱ ምግባረ ጥሩ ሳይሆን ግፈኛና ባለጌ ስለሆነ አባቱ ወደ ዳንሽዌ አባረረው ይባላል።
ቀዳሚው ዲ ዥዕ |
የኋሥያ ንጉሥ | ተከታይ ሹን |