ዳንጉን ዋንገም በኮርያ ልማዳዊ አፈ ታሪክ በኮሪያ በጥንት የነገሠ ንጉሥ ነበር። እርሱ ከሺንሺ መንግሥት (ፔዳል) ቀጥሎ የአዲስ መንግሥት መሥራች ሆነ። የዚህ መንግሥት ስም «ጆሰን» ሲሆን፣ በኋላ ዘመን (ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ም.) ሌላ «ጆሰን» የተባለ መንግሥት ስለ ኖረ፣ ዳንጉን የመሠረተው መንግሥት አሁን «ጥንታዊ ጆሰን» ወይም «ጎጆሰን» በመባል ይታወቃል። የፔዳል (ጸሐይ) ወገንና የናቱ ወገን «የድብ ጎሣ» በውሕደታቸው የጆሰን ብሔር ሆነው ዳንጉን እንደ ኮርያ መሥራችና አባት ይቆጠራል። ይህ በቻይና (ኋሥያ) ንጉሥ ያው 25ኛው ዓመት እንደ ሆነ ይታመናል።
ዋና ከተማው አሳዳል ምናልባት የአሁኑ ፕዮንግያንግ፥ ወይም ሓርቢን በማንቹርያ ነበር። ከዚህ በላይ ዳንጉን የራሱን አምልኮት እንደ ዐዋጀ ይባላል፤ እስከ ዛሬም ድረስ ዳንጉንን እንደ አምላክ የሚቆጠሩ አንዳንድ ትንንሽ ሃይማኖቶች በኮርያ አገር አሉ።
በጠቅላላ ለ93 ዓመታት (ወይም ለ1500 ዓመታት በአንድ ትውፊት) እንደ ነገሠ ይጻፋል። ከዚያ በኋላ ልጁ ቡሩ ተከተለው።
በ1903 ዓም. በኮሪይኛ የተዘጋጀው ዜና መዋዕል ኋንዳን ጎጊ ስለዚሁ አፈታሪካዊ ዘመን መረጃ ይሰጣል፤ ሆኖም በብዙ የኮርያ መምህሮች ዘንድ ይህ መጽሐፍ እንደ ትክክለኛ ታሪክ አይሆንም። ስለ ዳንጉን ዋንገውም ወይም ኢምግም ዘመን እንዲህ ይለናል። ዳንጉን ከአባቱ የሺንሺ ንጉሥና ከእናቱ የዉንግ ንግሥት ከልምጭ ዛፍ በታች ተወለደ (ምናልባት 2145 ዓክልበ. ግድም)። የአምላክ ምግባር ስለነበረው ሰዎች ሁሉ አከበሩት ታዘዙለትም፣ እድሜው 14 ዓመት ሲሆን፣ እናቱ የደዕብ ክፍላገር መስፍን አደረገችው። በ2108 ዓክልበ. ግድም የኮርያ ሰዎች (800 ሰዎች) በልምጭ ቦታ በሥነ ስርዓት ዙፋኑን ለዳንጉን ሰጡት። የሕዝቡ አለባበስ ያንጊዜ ከሣር ተሠራ፣ ጫማ ግን አልለበሱም ነበር ይላል። የዳንጉን ዐዋጅ እንዲህ ነበር፦
ከዚህ በኋላ ከሚኒስትሮቹ ፐንግ-ዉ ምድረ በዳ እንዲያቀና፣ ሰውንግጁ ቤተ መንግሥት እንዲያሠራ፣ ጎሺ በእርሻ ተግባር ላይ፣ ሺንጂ ምስሎችን እንዲፈጥር፣ ኪሰውንግ በሕክምና ጥናት ላይ፣ ነዑል ቤተሠቦቹን በዝርዝር እንዲዘግብ፣ ኸዊ እድሎችን (በንግር) በመናገር ላይ፣ ዉ በጦር ሠራዊት ላይ ሾማቸው።
በ2059 ዓክልበ. ግድም በታላቅ ጐርፍ ምክንያት የሕዝቡ ምቾት ተበላሸ። ስለዚህ ዳንጉን ሚኒስትሩን ፐንግ-ዉ ወንዞቹን እንዲገድብ አዘዘው። ሐውልት በ«ዉ» መንደር ተሠራ። በ2058 ዓክልበ. ሚኒስትሩን ፐዳል አምባ በሳምላንግ እንሲያሠራ አዘዘው። በ2042 ዓክልበ. ግድም አልጋ ወራሹን ልዑል ቡሩ በተልእኮ ወደ ዩ ላከው፣ ይህ ምናልባት በኋላ ዳ ዩ የተባለው የኋሥያ (ቻይና) አለቃ ይሆናል። በተጨማሪ ዳንጉን የ፭ ንጥረ ነገሮች ትምህርት አስተማረ፣ «ዩጁ» እና «ያንግጁ» ግዛቶችም ወደ ጆሰን ጨመረ። ዳንጉን ደግሞ «ኈዳይ»ን አሸንፎ ተገዥ አደረገው፣ ዩ-ሹን በተገዥነት አስተዳዳሪነቱን ሰጠው ይለናል። «ዩ-ሹን» ማለት የኋሥያ ንጉሥ ሹን ስም ነው፤ «ኈዳይ»ም በሻንዶንግ ልሳነ ምድር እንደ ነበር ይታስባል። በ2016 ዓክልበ. ግድም ለሀብቱ እድገት መስኖ፣ የሐር ትል፣ እና የአሣ ማጥመድ ሥራ ክፍሎች ወደ ጆሰን አስገባ። ዳንጉን ኢንገም በአገሩ ለ93 ዓመታት ነግሦ አረፈ፣ ልጁም ዳንጉን ቡሩ ያንጊዜ የጆሰን ዳንጉን (ንጉሥ) ሆኖ ተከተለው።