ዳግማዊ ዓፄ ኢያሱ

==

ዳግማዊ ዓፄ ኢያሱ
የዳግማዊ እያሱ አጽም ከእናቱ እቴጌ ምንትዋብና ልጁ ኢዮዋስ አጠገብ፣ ቁስቋም፣ ጎንደር
የዳግማዊ እያሱ አጽም ከእናቱ እቴጌ ምንትዋብና ልጁ ኢዮዋስ አጠገብ፣ ቁስቋምጎንደር
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ግዛት ጥቅምት ፲፪ ቀን ፲፯፻፮ እስከ ሐምሌ ፲፱ ቀን ፲፯፵፰ ዓ.ም.
ቀዳሚ በካፋ
ተከታይ ኢዮአስ
ሙሉ ስም ዓለም ሰገድ (የዙፋን ስም)
ሥርወ-መንግሥት ሰሎሞን
አባት በካፋ
እናት ምንትዋብ
ሀይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና

==

ዳግማዊ ኢያሱ (ጥቅምት 21፣ 1723 እ.ኤ.አ - ሐምሌ 27፣ 1755) በዙፋን ስማቸው ዓለም ሰገድ ከመስከረም 19፣ 1730 ጀምሮ እስከ እለተ ህልፈታቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩ ሲሆን አባታቸው አጼ በካፋ ሲሆኑ እናታቸው እቴጌ ምንትዋብ (የክርስትና ስም - ወለተ ጊዮርጊስ) ነበሩ።[1]

የወደፊቱ ዳግማዊ እያሱ ወደ ስልጣን በወጣበት ጊዜ ገና ህጻን ስለነበር እናቱ እቴጌ ምንትዋብ የልጁ እንደራሴ ሆና ተሾመች። ነገር ግን የልጁን መንገስ የሚፎካከሩ አካሎች የፋሲል ግቢን በመክበብ ጥቃት ማድረስ ጀመሩ። ስለሆነም ከጎጃም 30፣000 ሰራዊት ተነስቶ ጎንደር ስለገባ የስልጣን ተፎካካሪወች የፋሲልን ግቢ ጥሰው ውስጥ ሳይደርሱ ተሸነፉ.[2]። በዚህ ግርግር ምክንያት እቴጌ ምንትዋብ በእንደራሴነት ሳትወሰን እራሷ ላይ ዘውድ በመጫን ከልጇ ጋር እኩል ስልጣን እንዳላት አወጀች። በዚህ ሁኔታ የንግስትነት ማዕረግን ስትይዝ እቴጌ ምንትዋብ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ለመሆን በቃች።

የዳግማዊ ኢያሱ አስተዳደር

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ዳግማዊ ኢያሱ በ8 አመቱ ስልጣን ላይ የወጣ ሲሆን እንደ ታሪክ አጥኝው ፓውል ሄንዝ አባባል ከእናቱ ብዙ ምክርን ቢያገኝም እርሱ ግን ብዙ ጊዜውን አደን በማደንና የጎንደር ከተማን በተለያዩ ጌጣጌጦች በማስዋብ፣ ለውጭ አገር እጀ ጠቢባን ብዙ ገንዘብ በመክፈል፣ ከአውሮጳ የተለያዩ የቅንጦት እቃወችንና ትላልቅ መስታውቶችን በማስመጣት የአገሪቱን ጥሪት በማሟጠጡ በብዙወች ዘንድ ይነቀፍ ነበር[3] ። ሆኖም ግን በዚያው ዘመን ከአሁኑ ቼክ ሪፐብሊክ ተጉዞ በጎንደር ለ፩ ዓመት ቆይቶ የነበረው ሃኪም ሬሜደስ ፑትኪ በጊዜው እንዳስተዋለ በኢያሱ ዘመን ተከስቶ ለነበረው የንዋይ እጥረት ልጇን ሳይሆን እናቱን እቴጌ ምንትዋብን ተጠያቂ ያደርጋል። በፑትኪ አገላለጽ፣ ኢያሱ ገና ህጻን እያለ ንግስት እናቱ «"የአገሪቱን ግዛቶች ከፋፍላ ለተለያዩ ገዥወች ስለሰጠች ልጁ በዚህ ወቅት ለራሱ ተራ ወጭ የሚሆን በቂ ንዋይ እንኳ እንዳይኖረው ሆኗል"»። ፑትኪ በመቀጠል ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት፣ ኢትዮጵያ በነበረበት በ1752ዓ.ም.፣ ንግሱ ከእህቱ ጋር ከጎጃም በሚመጣ ገቢ ምክንያት እየተጣሉ እንደነበር ዘግቧል [4]

ከዚህ በተረፈ፣ ወጣቱ ንጉስ ፣ በ16 አመቱ፣ ከህዝቡ ዘንድ ከበሬታን ለማግኘት ሲል በሰናር መንግስት ላይ ዘመቻ አድርጎ በ1738ዓ.ም. በድንዳር ወንዝ ጦርነት ላይ በስናሮች የቆረጠ ራሱ ምስልና ግማደ መስቀሉ ተማረከ። ለኒህ ከፍተኛ ዋጋ ላላቸው ቅርሶች ማስመለሻ 8000 ትሮይ ኦንስ ወርቅ እንዲከፍል ተገደደ[5]። እንደ ታሪክ አጥኝው ዶናልድ ሌቪን አስተያየት ምንም እንኳ ለብዙ ዘመናት አመጽ የሚካሄድበትን ላስታን ዳግማዊ ኢያሱ በጦርነት ቢያረጋግም፣ በአጥባራ ወዝን አካባቢ በሚኖሩ ነገዶች ላይ ድልን ቢቀዳጅም ፣በድንዳር ወንዝ ጦርነት የገጠመውን ሽንፈት ሊያስተሰርይ አልቻለም [6]

በዚሁ ንጉስ ዘመን በተነሳ የአንበጣ መንጋና በኋላም በተነሳ ተላላፊ በሽታ በሺህ የሚቆጠሩ ሰወች አለቁ። አቡነ ክሬስቶዶሎስ ሲያርፉ ሌላ አዲስ አቡንግብጽ ለማስመጣት በቂ ነዋይ ታጣ። ከዚህ አንጻር በጎንደር የሚኖሩት ነገስታት ሃይል መዳከም ጀመረ። በላስታና በሸዋ እንዲሁም በትግሬ (የራስስሁል ሚካኤል መነሳት) ጠንካራም ባይሆን በለሆሳስ ራስ ገዝነት የመጀመረው በዚህ ንጉስ ጌዜ ነበር። የንጉሱ የቀደመ ሙሉ ሃይል በጎንደርጎጃም ተወስኖ ነበር[7]

እቴጌ ምንትዋብ

እቴጌ ምንትዋብ ከአማቷ፣ ሮማነወርቅ( የአጼ በካፋ እህት) ፣ ልጅ ምልማል እያሱ ጋር የምታደርገውም ግንኙነት ዳግማዊ እያሱን እጅግ ያስቆጣ ነበር። እቴጌ ምንትዋብ ከዚህ ከምልምል እያሱ ዘንድ 3 ልጆን ሴት ልጆችን ስታፈራ ከነዚህ ውስጥ አንዷ ወይዘሮ አስቴር ኢያሱ በመባል በቁንጅናዋ በታሪክ የምትታወቀው ነበረች። የእቴጌ ምንትዋብ ከአማቷ ልጅ ጋር መማገጥ በዘመኑ እጅግ ትልቅ ነውር የነበር ቢሆንም ንጉሱ ግማሽ እህቶቹን ይንከባከብ ነበር። አባታቸውን ግን ከመጥላቱ የተነሳ በ1742 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ከጣና ሃይቅ ዳርቻ ካለ ገደል ተወርውሮ እንዲሞት እንዳደረገ ይታመናል.[8]

ዳግማዊ እያሱ ግንቦት 1755 ላይ በጸና ታመው በሚቀጥለው ወር ሞቱ። የምልማል እያሱ እህት በወንድሟ ሞት ንዴት መርዝ ሰጥታው እንደገደለቸው በጊዜው የታመነ ጉዳይ ነበር። እቴጌ ምንትዋብም ልጇን ለማስቀበር ከግምጃ ቤት ንዋይ ብትፈልግ ከጥቂት ዲናሮች በስተቀር ካዝናው ባዶ ሆኖ ተገኘ። በዚህ ያዘነቸው ምንትዋብ ሁሉን ትታ በቁስቋም ወዳሰራችው ቤተመንግስቷ ሄዳ ከጎንደር ለመራቅ ዛተች። ሆኖም ግን ጥቂት መኳንንት የልጅ ልጇ ኢዮአስ እንደራሴ ሆና እንድትቀጥል አሳመኗት።[9]

  1. ^ ሪቻርድ ፐንክኸርስት, "An Eighteenth Century Ethiopian Dynastic Marriage Contract between Empress Mentewwab of Gondar and Ras Mika'el Sehul of Tegre," in Bulletin of the School of Oriental and African Studies, 1979, p. 458.
  2. ^ Donald N. Levine, Wax and Gold: Tradition and Innovation in Ethiopian Culture (Chicago: University Press, 1965), p. 24. Details from Remedius Prutky's account in J.H. Arrowsmith-Brown (trans.), Prutky's Travels in Ethiopia and other Countries with notes by Richard Pankhurst (London: Hakluyt Society, 1991), pp. 173f
  3. ^ Paul B. Henze, Layers of Time (New York: Palgrave, 2000), p. 106
  4. ^ Prutky's Travels, p. 306
  5. ^ E. A. Wallis Budge, A History of Ethiopia: Nubia and Abyssinia, 1928 (Oosterhout, the Netherlands: Anthropological Publications, 1970), pp. 454f.
  6. ^ Levine, Wax and Gold, p. 24
  7. ^ Edward Ullendorff, The Ethiopians: An Introduction to Country and People, second edition (London: Oxford Press, 1965), p. 81
  8. ^ ተክለ ጻድቅ መኩሪያየኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት
  9. ^ The Royal Chronicle of his reign is translated in part by Richard K. P. Pankhurst, The Ethiopian Royal Chronicles (Addis Ababa: Oxford University Press, 1967).