ጋልባ

ጋልባ የሮሜ ቄሣር

ሴርዊዩስ ሱልፒኪዩስ ጋልባ ለአጭር ዘመን ለ፯ ወር ከሰኔ ወር 60 ዓም ጀምሮ የሮሜ መንግሥት ቄሣር ነበር። የአራቱ ቄሣሮች ዓመት መጀመርያው ንጉሥ ነበረ።

ጋልባ በ10 ዓክልበ. በጣልያን ተወለደ። በሮሜ ግቢ፣ ነገሥታት አውግስጦስጢቤርዮስ እንደ ጎበዝ ወጣት ቆጥረውት ወደ ፊት ትልቅ ይሆናል እንዳሉ ተጽፏል። በነገሥታት ሰዶማዊ ኑሮ ዘዴ ልጆች አልወለዱም ስለ ነበር፣ አልጋ ወራሽ ምንጊዜም የተወደደው ጎረምሳ እንደ ንጉሥ ዕንጀራ ልጅ ነበር።

ጋልባ በ12 ዓም በሥራዊት የፕራይቶር ማዕረግ አገኘ፣ ለ25 ዓም ቆንሱል ሆኖ ተመረጠ። በ53 ዓም ንጉሥ ኔሮንሂስፓኒያ ታራኮነንሲስ ክፍላገር (ምሥራቅ ስፔን) አገረ ገዥ አድርጎ ሾመው።

የጋልባ መሀለቅ

ጋሊያ ሉግዱኔንሲስ (ፈረንሳይ) አገረ ገዥ ጋዩስ ዩሊዩስ ዊንዴክስ በኔሮን ማባከንና አምባገነንነት ተቀይሞ በ60 ዓም ዓመጸበት። በኔሮን ፈንታ ጋልባ የተሻለ ቄሣር ለማድረግ አሰበ። የኔሮን ጌርማኒያ ሥራዊት አለቃ ሉኪዩስ ዌርጊኒዩስ ሩፉስ ግን በውግያ ዊንዴክስን አጠፋው። ከዚህ በኋላ የዌርጊኒዩስ ሥራዊት እሱን በኔሮን ፈንታ ይደግፍ ነበር፤ ዌርጊኒዩስ ግን የትም አልገሠገሠም። ጋልባ ከኔሮ ይሻለናል የሚል ስሜት ከፈረንሳይና ከስፔን ይልቅ ወደ ጣልያን እራሱ ሲስፋፋ፣ የኔሮን ሥልጣን እየጠፋ፣ በመጨረሻ ኔሮን ራሱን ገደለና ጋልባ ወደ ሮሜ ገሥግሦ ወዲያው ቄሣር ተደረገ።

ከዚህ ብሔራዊ ትግል ቀጥሎ ጋልባ የማይቀበሉትን ብዙ ገደለ፤ ወይም በገብር ሸከማቸው፤ በአጠቃላይ ጨካኝ አመራር ተከተለ። በእርጅናው ደግሞ ሦስት ወንድ ተወዳጆች በእውነት እንደ ገዙት ይባል ነበር።

በሚከተለው ጥር ወር የጌርማኒያ ሥራዊት በጋልባ ላይ አመጹበትና የጌርማኒያ አገረ ገዥ ዊቴሊዩስ ንጉሥ እንዲሆን አዋጁ። ጋልባ በሮሜ ቆይቶ አልጋ ወራሹ ሉኪዩስ ካልፒኒዩስ ፒሶ እንዲሆን ሰየመው። በዚህ የሉሲታኒያ (ፖርቱጋል) አገረ ገዥ ኦጦ በተለይ ተናደደ፣ አልጋ ወራሽነቱን ለራሱ መኝቶ ነበርና። የሮሜ ሥራዊት ደግሞ ኦጦን ደገፈውና በጋልባ ላይ አመጹ። ጋልባ በድካምነቱ በቃሬዛ ተሸክሞ ሲቀርብላቸው ገደሉትና ያንጊዜ ኦጦ ለአጭር ወራት በፈንታው የሮሜ ቄሣር ሆነ።