ጥንታዊ እንግሊዝኛ (Englisc /ኧንግሊሽ/) በእንግሊዝ አገር ከ440 ዓ.ም. ገደማ እስከ 1100 ዓ.ም. ያሕል የተናገረ ቋንቋ ነበር። ዛሬ ጀርመንና ዴንማርክ ከተባሉት አገሮች ፈልሰው በእንግሊዝ በተስፈሩት ሕዝብ የተናገሩበት ሲሆን የዘመናዊ እንግሊዝኛ ቀድሞ አይነት ነው። ሆኖም በቃላትም ሆነ በስዋሰው ከዘመናዊ እንግሊዝኛ በጣም ይለያል። ቅርብ ዘመዶቹ ጥንታዊ ፍሪዝኛ እና ጥንታዊ ሴክስኛ ናቸው።
ጥንታዊ እንግሊዝኛ በርካታ ተመሳሳይ ቀበሌኞች ነበሩት። በተለይ በስሜን እንግሊዝ የኖሩት የአንገሎች መነጋገርያ በደቡብ ከኖሩት ከሴክሶች ትንሽ ተለያየ።
ከ800 ዓ.ም. ገደማ ጀምሮ ስሜኑ በቫይኪንጎች ስለተወረረ በንጉስ አልፍሬድ ጊዜ የሴክሶች ቀበሌኛ ይፋዊ ሁኔታ አገኘ። ቢሆንም የቫይኪንጎች ቋንቋ ኖርስኛ ከጥንታዊ እንግሊዝኛ ጋር ዝምድና ነበረውና ከኖርስኛ አያሌው ቃላት ወደ እንግሊዝኛ ገቡ። ለምሳሌ የእንግሊዝኛ ቃላት sky /ስካይ/ (ሰማይ) leg /ለግ/ (እግር) እና they /ዘይ/ (እነሱ) የደረሱ ከኖርስኛ ነበር። በእንግሊዝ ኗሪዎች ቋንቋ (በጥንታዊ እንግሊዝኛ) እነዚህ ቃላት 'ሄዮቮን'፣ 'ሽያንካ' እና 'ሂዬ' ሆነው ነበር።
የተማሩ ሰዎች (መምህራን ወይም ቄሶች) በብዛት የሮማይስጥ ዕውቀት ስለነበራቸው ደግሞ ከሮማይስጥ ተጽእኖ አንዳንድ ቃላት የዛኔ ወደ እንግሊዝኛ ገቡ። ንጉሥ አልፍሬድ እራሳቸው ብዙ መጻሕፍት ከሮማይስጥ አስተረጎሙ።
ኖርማኖች እንግሊዝን በ1059 ከወረሩ ጀምሮ እንግሊዝኛ ከትምህርት ቤት ስለ ተከለከለ በየጥቂቱ ባሕርዩ እጅግ ተለወጠ።
በጥንታዊ እንግሊዝኛ እያንዳንዱ ስም የተወሰነ ጾታ (ወንድ፣ ሴት ወይም ግዑዝ) ነበረው። ለምሳሌ sēo sunne /ሴዮ ሱነ/ (ፀሐይቱ) አንስታይ፣ se mōna /ሴ ሞና/ (ጨረቃው) ተባዕታይ፣ þæt wæter /ዛት ዋተር/ (ውኃው) ግዑዝ ነበር።
ቋንቋው መጀመርያ ፉሶርክ በተባለው የሩን ፊደል ሲጻፍ ክርስትና ከተቀበለ በኋላ ግን በላቲን አልፋቤት ሊጻፍ ጀመረ። አንዳንድ ተጨማሪ ፈደላት እንዲህ ነበሩ: