ፌኒየስ ፋርሳ

ፌኒየስ ፋርሳ Fenius Farsa (ወይም Farsaid ፋርሳይድ) በአይርላንድ አፈ ታሪክ የእስኩቴስ ንጉስ ነበሩ። የኦጋም ጽሕፈትና የጎይደልክ ቋንቋ የፈጠሩ እንደ ነበሩ ይባላል። («ጎይደልክ» የአይርላንድና የስኮትላንድ ጥንታዊ ቋንቋ ነው።)

በ11ኛ መቶ ዘመን በወጣው መጽሐፍ ሌቦር ጋባላ ኤረን ዘንድ፣ ለናምሩድ የባቢሎን ግንብ ከሠሩት 72 አለቆች አንድ ሆነው ግንቡ ከወደቀ በኋላ ወደ እስኩቴስ ተጓዙ።

ደግሞ በአውራከፕት ና ኔከሽ በተባለው ጥንታዊ መጽሐፍ ዘንድ ፌኒየስ ከጒደል ማክ ኤሆር፣ ከያር ማክ ኔማና ከ72 ሊቅውንት ጋራ ከእስኩቴስ ተጓዙ። በናምሩድ ግንብ በኩል የተደባለቁትን ልሣናት ለማጥናት ወደ ሰናዖር ሜዳ ደረሱ። ነገር ግን ከዚያ አስቀድሞ እንደ ተበተኑ አገኝተው፣ ፌኒየስ 72ቱን ሊቃውንት ቋንቋዎቻቸውን እንዲያጥኑ ወደ ተበተኑት ሕዝቦች ልከው በግንቡ ሥፍራ ቆይተው ሥራውን አስተባበሩ። ከ10 አመታት በኋላ ትንትናው ተፈጽሞ ከተደባለቁት ልሣናት የተሻለውን መርጠው «ምርጥ ቋንቋ» ፈጥሮ በጓደኛው ጒደል ስም ቋንቋውን «ጎይደልክ» አሉት። ደግሞ ኦጋም የሚባል ጽሕፈት ፈጠሩለት።