ፍሬገ

ፍሬገ

ጎትሎብ ፍሬገ (Friedrich Ludwig Gottlob Frege ) (1848 - 1925) ጀርመናዊ ፈላስፋስነ አምክንዮ ተመራማሪ፣ እና ሂሳብ አጥኝ ነበር። ፍሬገ ከጥንቱ ግሪካዊ አሪስጣጣሊስ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአምክንዮ ትምህርት ሙሉ በሙሉ የለወጠና ፕሪዲኬት ካልኩሉስ የተባለውን የአምክንዮ ርዕዮት አለም ያበረከት ነው። በዚህ አዲሱ አምክንዮ ስርዓት የተወሰኑ አባባሎች እንዴት በአምክንዮ እንደሚፈቱና አንድን ማረጋገጫ (proof) በርግጥ ትክክል ነው የሚባልበትን ስልት ያቋቋመ ነው። ከዚህ በመነሳት ማናቸውም የሂሳብ ርዕዮቶች ወደ ቀልል ያሉ የአምክንዮ አባባሎች እንደሚቀየሩ ማሳየት ችሏል። ምንም እንኳ አጠቃላዩን የሂሳብ ትምህርት ወደ ስነ-አምክንዮ ለመቀየር ያደረገው ሙከራ በአንዲት ያልተረጋገጠች ዕውነታ (axiom) ምክንያት በተነሳች ስርዓታዊ ቅራኔ ለውድቀት ቢበቃም ስለ ትርጉም እና ስለ ዘዴ ባቀረበው ጥናቱ ግን እስካሁን የሚሰራባቸውን እውነታወች ለማግኘት ችሏል። ስለቋንቋም ያስቀመጠው አጠቃላይ ርዕዮት እስካሁን ድረስ በፈላስፎች ሲሰራበት ይገኛል። ሆኖም ግን ህይወቱን በሙሉ ሂስባን ወደ ስነ-አምክንዮ የመቀየር ትልሙ ሳይሳካለት ቀርቷል።