ሸዋ በኢትዮጵያ ገጸ ምድር መሃል ላይ የሚገኝ ታሪካዊ ክፍለ ሃገር ነው። ሸዋ ከአምስቱ ዋና ክፍለ ሃገራት ማለትም የሃበሻ ምድር ውስጥ አንዱ ነው፤ በኢትዮጵያ ጥንት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያለው ስፍራ ነው። ለብዙ መቶ ዓመታት በሉዐላዊነት በራሱ መሪዎች ሲተዳደር የኖረ የኢትዮጵያ አካል ሲሆን፣ ርዕሰ ከተማው እስከ ፲፰፻፹፱ ዓ/ም በሰሜን ሸዋ ውስጥ በየጊዜው በተለያዩ ሥፍራዎች ሲፈራረቅ ቆይቶ ባለፉት መቶ በላይ ዓመታት ግን አዲስ አበባ ሆናለች። ደብረ ብርሃን፤ አንኮበር፤ ተጉለት አንጾኪያ፤ ልቼ እና እንጦጦ በተለያዩ ጊዜያት የሸዋ ርዕሰ ከተማዎች ነበሩ። የሸዋ ገጸ ምድር እምብርት ባሁኗ ኢትዮጵያ መሃል የሚገኙት ተራራዎች ናቸው። በአህመድ ግራኝ ወረራ ጊዜ የባሌ ክፍለ ሀገር ከተወሰደ በኋላ የሸዋ ድንበር የኢትዮጵያ የደቡብ-ምሥራቅ ድንበር ነበር። የግዛቱ ተራራማነት የተፈጥሮ መከላከያ በመሆን ከውጭ ወረራ ለመላ አገሪቱ ደጀን የነበረና በፍትህ የአስተዳደር ዝናውም ለሌላ የኢትዮጵያ ዜጋዎች መጠጊያና መሸሸጊያም ነበር። አንዳንዴም በወራሪ ሕዝቦች ምክንያት ከቀሪው የኢትዮጵያ ግዛቶች ተግንጥሎም አብዛኛው የሰሜን ሸዋ ግዛቶች፣ ማለትም ሰላሌ(ግራሪያ)፤መርሃቤቴ፤ ደራ፤ መንዝ፤ ተጉለት፤ ይፋት፤ ምንጃር እና ቡልጋ ሕዝብ ክርስቲያን አማራ ናቸው። ደቡብ እና ምሥራቅ ሸዋ ውስጥ ግን አብዛኛው የኦሮሞ ብሔር እና የእስላም ኃይማኖት ተከታዮች ናቸው ባሁን ላይ የሚገኙት። በሰሜን ሸዋ ብዙ ታሪካዊ አብያተ ክርሲያናት እና ገዳማት ይገኛሉ። ከነዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው፣ አቡነ ተክለ ኃይማኖት በሰላሌ ወረዳ(ግራርያ) የመሠረቱት ታዋቂው የደብረ ሊባኖስ ገዳም ይገኙበታል።
ግራርያ Famous : Danny Mack
ግራርያ ታዋቂ ሰው : Danny Mack
ሸዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ የተመዘገበችው በ896 እ.ኤ.አ. በተመሠረተውና ዋና ከተማውን ወለላ (Walalah)ላይ አድርጎ በነበረው የእስላም ግዛት ውስጥ ነው በማለት በኢትዮጵያ ታሪክ ዘጋቢዎች ይታመናል። ከነዚህም አንድ፣ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ትምህርታዊ መጽሐፍትን የደረሰው ሀንቲንግፎርድ (G.B.W. Huntingford) ነው። ይህ ግዛት ወደ ፲፪፻፸፮ ዓ/ም በይፋቱ ሱልጣን ሥር ተጠቃለለ። በቅርብ ጊዜ በፈረንሳይ የሥነ-ቅርስ ባለሙያዎች ጥናት መሠረት ሦስት ቦታዎች የሸዋ እስላማዊ ንጉዛት(በዘውድ የሚተዳደር ግዛት) የከተማ ማእከላት ናቸው ተብለው ተገምተዋል።
አጼ ይኩኖ አምላክ የዘመኑን የዛግዌ ስርወ መንግሥት በመቃወም ሲነሱ ከክርስቲያን አማራዎች አገር ከሸዋ እንደተነሱ እና ቀድሞውንም የአክሱም ነገሥታት በጉዲት መነሳት ሥልጣናቸውን ሲለቁ ከዛች ንግሥት በመሸሽ ተከታዮቻቸውንና ቤተ ሰባቸውን ደብቀው የኖሩት በዚሁ በሸዋ ውስጥ ነበር። እንዲሁም ክብረ ነገሥት (አንቀጽ 39) እንደሚለው፣ ሸዋ የአጼ ቀዳማዊ ምኒልክ ክፍላገር ሆኖ ነበር። ሆኖም አንዳንድ ዘመናዊ ሊቃውንት የዳማትና የአክሱም መንግሥታት ሥልጣን እስከ ሸዋ ድረስ ወደ ደቡብ እንዳልተዘረጋ የሚል ጥርጣሬ አለባቸው።
በ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መላው ክርስቲያን ኢትዮጵያ በአህመድ ግራኝ ሠራዊት (አዳል) በተወረረ ጊዜ ሸዋ ተመልሶ የእስላም አገር ሆነ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ ፲፰ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የሸዋ ታሪክ እምብዛም ባይዘገብም አጼ ልብነ ድንግል እና ልጆቻቸው በወረራ ጊዜያት ሸዋን መሸሻቸው አድርገውት እንደነበር ተጽፏል።
የሸዋ ነገሥታት ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት በይኵኖአምላክ ጊዜ ከደብረ ሊባኖስ ወደ ሐይቅ በመጡት በአባ ተክለሃይማኖት እገዛ እንደተመሠረተ ይታመናል። የአኵስም ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት በዮዲት ጕዲት ተንኮታኩቶ ወደመጥፋት ደርሶ ነበረ። የዮዲት ጕዲት ጦር በሸዋ ጭፍሮች ከተሸነፈ ወዲህም ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት አላንሰራራም ነበር። ይኵኖአምላክም ከንግሥናው በፊት በይፋት፣ በመርሐ ቤቴ፣ በተጕለትና በመንዝ ኖሯል። ከይኵኖአምላክም ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ውስጥ 99 ሀገራትን (በሓውርት) ያስገበረው ዓምደ ጽዮን ደማቅ ታሪክ ካላቸው ነገሥታት መሃል አንዱ ነው። ከግራኝ ይማም አሕመድ በኋላ ጎንደር መናገሻ ከመሆኗ ጋራ ተያይዞ የሸዋ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ለጎንደሩ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት መሠረት ሆኗል። ከዚያም በኋላ በ17ኛው ክ/ዘመን ነጋሢ ይፋት አካባቢ ያለውን ቦታ ይቆጣጠር ጀመር። በይፋዊ ታሪክ፣ የነጋሢ አባት ልብሰ ቃል (በመንዝ የአጋንቻ ጌታ) በአጼ ልብነ ድንግል ታናሽ ልጅ በያዕቆብ በኩል የሚመጣ በአባት በኩል የዘር ሐረግ ያለው ነው ይላል። ይህም ማለት ከሰለሞን ስርወ መንግስት ጋር የተያያዘ ነው ማለት ነው። በዚህ መሰረት የጎንደር ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ከሸዋ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት በኋላ የመጣና ያበበ ነው ማለት ይቻላል።
የሸዋ መሪዎች ማዕረጋቸው ደግሞ በሸዋ ብቻ የሚገኘው መርዕድ አዝማች ነበር። የነጋሢ ልጁ ስብስትያኖስ የመጀመሪያው መርዕድ አዝማች ነበር። ተከታታይ መሪዎች ይሄንን ማዕረግ ሲጠቀሙበት ቆይተው የመርዕድ አዝማች ወሰን ሰገድ ልጅ ሣህለ ሥላሴ በአባታቸው ወንበር ሲቀመጡ ንጉሠ ሸዋ ተባሉ። ከሳቸውም በኋላ ልጃቸው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ለስምንት ዓመታት ነግሠው ጥቅምት ፴ ቀን ፲፰፻፵፮ ዓ/ም ሲያርፉ ልጃቸው አቤቶ ምኒልክ ገና ሕጻን ነበሩ። ወዲያው በዓፄ ቴዎድሮስ ተማርከው መቅደላ ከኖሩ በኋላ አምልጠው ሸዋ ሲገቡ በአባታቸው ወንበር ንጉሠ ሸዋ ተብለው ነገሡ።ከርሳቸው በኋላ ቀዳማዊ ግርማዊ ኃይለ ሥላሴ የሸዋ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት የመጨረሻው ንጉሥ ናቸው። በ፲፱፻፳፫ ዓ/ም የንጉሠ ነገሥትነቱ በትረ ሥልጣን ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲዘዋወር፤ አልጋ ወራሽነቱን እና የጥንቱን የሸዋ መሳፍንት ማዕርግ ለልጃቸው አስፋ ወሰን ሰጥተዋቸው ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን ተባሉ።
በተለምዶ የሸዋ አማርኛ የሚባለው ርቱዕ አማርኛ ነው። አሁን ላይ በመላው የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት ቅቡልነት አግኝቷል። ለአማርኛ መዝገበ ቃላት መዳበርም የሸዋ ሊቃውንት የማይተካ ድርሻ አበርክተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የቆየ ታሪክ ካላቸው አካባቢዎች አንዱ የሰሜን ሸዋ ዞን ነው፡፡ ፲፭ሺ ፱፻ ነጥብ ፺፯ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የሰሜን ሸዋ ዞን በሁለት የከተማ አስተዳደሮችና በሃያ ሁለት ወረዳዎች ተከፋፍሎ ፪ ነጥብ ፫ ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርበት ሲሆን ውርጭ፣ ቆላ፣ ደጋና ወይና ደጋ የአየር ንብረቶችን አካቶ ይዟል። አዋሳኞቹም በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ክልል፣ በሰሜን ምስራቅ አፋር፣ በሰሜን ደቡብ ወሎና ኦሮሚያ ዞኖች ናቸው።
ዞኑ ከቅድመ ታሪክ ጀምሮ እስከ ታሪክ ዘመን ያሉ አሻራዎች የሚገኙበት ስለመሆኑ የሥነ ቅርስ ግኝቶች ይጠቁማሉ። ከ፲፪፻፸ ዓ/ም እስከ ፲፭፻፳፯ ዓ/ም ድረስ «የሰሎሞን ስርወ መንግሥት» የመራሄ መንግሥቱ ዋና ማዕከል እንደነበረም የተለያዩ የታሪክ ምንጮች ይገልፃሉ። የሰሜን ሸዋ ምሥራቃዊ ክፍል ከ፰፻፸፪ ዓ/ም ጀምሮ ዋነኛው የእስልምና ስርወ መንግሥት መቀመጫ ከመሆኑ ባሻገር ከ፲፪ኛው እስከ ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የይፋት ስርወ መንግሥት የማዕከላዊ መንግሥቱ ተቀናቃኝ ኃይል እስከመሆን ደርሶ ነበር። በመጨረሻም ከሌሎች ታሪካዊ ሁኔታዎች ጋር ተደማምሮ በ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስልምናው ኃይል በግራኝ አህመድ መሪነት በማየሉና በማሸነፉ ማዕከላዊ መንግሥቱ ከሸዋ ወደ ጎንደር ለመዛወር ተገዷል።
በ፲፮፻፺፮ ዓ/ም በመንዝ የተንቀሳቀሰው የሸዋ ስርወ መንግሥት እንደገና ማዕከላዊ መንግሥቱ ወደ ሸዋ በመመለሱ በዘመናዊ ታሪካችን ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በእነዚህ የታሪክ ሂደቶችም ሰሜን ሸዋ የበርካታ ጥንታዊ የታሪክና የባህል ነፀብራቅ የሆኑ አሻራዎች ባለቤት ሊሆን ችሏል።
ሰላ ድንጋይ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የትውልድ ሥፍራም ናት። በእናታቸው በወይዘሮ ዘነበወርቅ እንደተሰራችና በስማቸውም የምትጠራው ሰገነት ከተሰራች ብዙ ዘመናት አስቆጥራለች። ሰላ ድንጋይ የአብዛኛዎቹ የሸዋ ነገሥታት ሚስቶችና እቁባቶች መቀመጫ ስለነበረች የወይዘሮዎች ከተማ በመባልም ትታወቃለች።
በቅድስቱ ግድግዳ ላይ የተሳሉት ጥንታዊ የፈትል ስእሎች ከመንፈሳዊ መግለጫነት ባሻገር ደጃዝማች ምኒሊክ በልጅነታቸው በዓፄ ቴዎድሮስ ሲማረኩ፣ በ፲፰፻፶፯ ዓ.ም ከመቅደላ ሲያመልጡና በኋላም በፍቼ ከተማ ከዓፄ ዮሐንስ ጋር ያካሄዱትን ስምምነት የሚገልጹ ናቸው። በመካነ ፈውስነቱ በአገራችን ስሙ እየገነነ የመጣው የሸንኮራ ዮሐንስ ፀበልም የሚገኘው ከባልጭ ከተማ የአሥራ አምስት ደቂቃ የእግር ጉዞ በኋላ ነው። ፀበሉ ቀደም ሲል በሽተኞችን ያድን እንደነበር ይነገር እንጅ ቀሳውስትና የፀበሉ አስተዳዳሪዎች ግን ከ፲፱፻፶፯ ዓ.ም ጀምሮ ዝናው እንደታወቀ ይናገራሉ። ፀበሉ የሚገኝበት አካባቢ ዳገታማና ቁልቁለት በመሆኑ ከአዲሱ ዩሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አጠገብ ሆኖ ሲመለከቱት የአካባቢውን አስደናቂ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና በተፈጥሮ ውበት የታደለውን የመስህብ ሥፍራ ማየት ያስደስታል።
“ሙሽራ ድንጋዮች” በገድሎ ሜዳ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ የሚገኙ የሰው ቅርጽ ያላቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው። ትክል ድንጋዮቹ ቆመውና ካሉበት ሳይነሱ የሚገኙ ፳፩፣ በሥፍራው ወድቀው የሚገኙ ፪፣ ከሥፍራው ተነስተው ገበሬዎች ለእርሻ ድንበር መለያ የተጠቀሙባቸው ፵፬ ናቸው። የሙሽራ ድንጋዮች ስያሜቸውን ያገኙበት በአንድ ወቅት በመንገድ ላይ እያሉ ሙሽሮችና ሠርገኞች ባደረጉት ከልክ ያለፈ ጭፈራ እግዚአብሔርን በማሳዘናቸው ተረግመው ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ ወደ ድንጋይነት ተቀይረው በዚያው እንደቀሩ ይነገራል።
የሙሽራ ድንጋዮች ታሪካዊ አመጣጥ ከላይ በተገለጸው አኳኋን የተለየ ጥንታዊ ሰዎች ለአንድ ዓላማ ያቆሟቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው ተብሎ ይታመናል። ምናልባትም ከአክሱም ዘመን በፊት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ የእደ ጥበብ ውጤት እንደሆነ ይገመታል። የሙሽራ ድንጋዮች በአብዛኛው ከደቡብ ኢትዮጵያ የጥያ ትክል ድንጋዮች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። እነዚህ ምስጢርን ያዘሉ የታሪካችን አሻራዎች ለጥናትና ምርምር የሚጋብዙና ለተመልካች ደግሞ የሚያዝናኑ ናቸው።