ደብረ ሊባኖስ

ደብረ ሊባኖስ
ደብረ ሊባኖስ በአጼ ኃይለ ስላሴ እንደተሰራ
ደብረ ሊባኖስ is located in ኢትዮጵያ
{{{alt}}}
ደብረ ሊባኖስ

9°43′ ሰሜን ኬክሮስ እና 38°52′ ምሥራቅ ኬንትሮስ


ደብረ ሊባኖስ በጥንቱ ግራርያ አውራጃ (በአሁን ስሙ ሰላሌ ) ሸዋ የሚገኝ ጥንታዊ ገዳም ነው። ገዳሙ በመጀመሪያ ደብረ አስቦ ሲባል የአሁን ስሙን የያዘው በአጼዘርዓ ያዕቆብ አነሳሽነት በ፲፬፴፯ ዓ.ም ነው።

ስለገዳሙ ምሥረታ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል መሠረት፣ ይህ ገዳም የተመሰረተው በ1300ዎቹ መጀመሪያ በራሳቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ነበር። ተክለ ሃይማኖት የግራርያን ስዩም የነበረውን ሰሜን ሰገድን ክርስትና እንዲቀበል ካደረጉ በኋላ፣ ይሄው ሹም ለተክለ ሃይማኖት አስቦ ከተባለው ስፍራ መሬት ለክርስትና ግልጋሎት በፈቃድ ስለሰጠ፣ በዚሁ ቦታ ለቅድስት ማሪያም መታወሻ የሚሆን ቤ/ክርስቲያን ተቋቋመ። [1] ይህ በንዲህ እንዳለ በ15ኛው ክፍለ ዘመን የቤ/ክርስቲያኑ ቄስ ገበዝ ቴዎድሮስ ለራሳቸው ለጻዲቁ አቡነት ተክለ ሃይማኖት መታሰቢያ የሚሆን ቤ/ክርስቲያን አስገነቡ። ይህ ቤ/ክርስቲያን እስከ ተገነባ ድረስ ቀሳውስቱ በአካባቢው ዋሻወች ይኖሩ እንደነበር ትውፊት አለ።

ከ15ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የደብረ ሊባኖስ መሪዎች በእጨጌ ማዕረግ የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን ገዳም ስርዓት መሪ ሆኑ። ከ1437 ጀምሮ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ለገዳሙ አዲስ ስም በማውጣት ደብረሊባኖስ ካሉት በኋላ፣ ለቤተ ክርስቲያኑ መሬትን በመስጠት ገዳሙ እራሱን እንዲችል አድርገዋል [2] በዚሁ በ15ኛው ክፍለ ዘመን አዳዲስ መጻህፍት በደብሩ ታተሙ። ከነዚህ ውስጥ ገድለ ተክለ ሃይማኖትገድል ፊልጶስመጽሐፈ ፍልሰቱ ለተክለ ሃይማኖት ይገኙበታል።

ስለ ገዳሙ ማህበረ ሰብ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ምንም እንኳ በ1524ዓ.ም. ይህ ገዳም በግራኝ አህመድ ቢፈርስም፣ የገዳሙ ማህበራዊ ስርዓት ግን ሳይፈረስ ቀጥሏል። ሆኖም በጊዜው የነበሩት የደብረ ሊባኖሱ እጨጌ ዮሐንስ ከአጼ ገላውዲዎስ ጋር ኑር ሙጋህድን ሲዋጉ፣ 1551ዓ.ም. ላይ አረፉ። ከዚህ በኋላ አጼ ሠርፀ ድንግል ገዳሙን የአገሪቱ የሃይማኖት ማዕከል ለማድረግ ቢሞክሩም ኋላ ላይ የብዙ ኦሮሞ ቡድኖች አካባቢውን ስለወረሩትና ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል ስለተለያየ ሳይሳካ ቀረ። በእጨጌ ዘረ ወንጌልና እጨጌ አብርሃም ዘመን የደብረ ሊባኖስ ማህበረሰብ ጓዙን በመጠቀለል ወደ ጣና ሃይቅእንፍራዝተሰደደ። በዚህ መሰረት ቤተ ተክለ ሃይማኖት፣ በአዘዞጎንደር ተቋቋመ። ይሄውም በአሁኑ ዘመን አዘዞ ተክለ ሃይማኖት የሚባለው ነው። ይህ ማህበረሰብ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ግራርያ ላይ ጉብኝት በማድረግ የደብረ ሊባኖስን ገዳም እንደገና ከማቋቋሙም በላይ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ለማግኘት ችሏል።

ስለ ገዳሙ ሕንፃ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የገዳሙን ዋና ሕንፃ ከኢትዮጵያ ነገሥታት ብዙዎቹ ያማረ በመሰላቸው፤ ጊዜያቸው በፈቀደላቸው ጥበብ ሕንፃውን አሠርተዋል። ለምሳሌ፤ የመጀመሪያውን ሕንፃ ያሳነፁት በ፲፪፻፷ የነገሡት አጼ ይኩኖ አምላክ ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ በ፲፬፻፭ ዓ/ም የነገሡት አጼ ይስሐቅ ነበሩ። እንዲሁም በ፲፰፻፬ ዓ/ም በወሰን ሰገድ፣ በ፲፰፻፸፮ ዓ/ም አጼ ዮሐንስ፣ በ፲፱፻ ዓ/ም በዳግማዊ ምኒልክ እንደገና ታንጿል።

የሥፍራው ገደላማ አቀማመጥ እና የአፈሩ የመሸሽ ባህሪ ለሕንጻው የማይስማማ በመሆኑ ግንቡ ለብዙ ጊዜ ሊያገለግል አልቻለም።

በመጨረሻ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ ከጥልቅ የግንባታ ጥናት በኋላ ተሠርቶ ኅዳር ፱ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ/ም ቅዳሴ ቤቱ ተመረቀ።

ንጉሠ ነገሥቱ የጣልያንን ጦር ለመግጠም በደሴ በኩል ወደማይጨው ሲዘምቱ፤ እግረ መንገዳቸውን ገዳሙን ለመጎብኘት ኅዳር ፲፮ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ/ም ሄደው ለእጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ (በኋላ አቡነ ባስልዮስ) ወንጌል ላይ “በገንዘብ የማትገዛ አምላክ መሆንህን አምናለሁ፤ ያንተ ያልሆነ የለኝምና…” የሚል ቃል ጽፈው ሰጧቸው።

ፋሺስት ኢጣሊያ ድሉን ከተቀዳጀች በኋላ በጨካኙ ማርሻል ግራዚያኒ ትዕዛዝ በ፲፱፻፳፱ ዓ/ም የገዳሙ የገዳሙ መነኮሳት ሲጨፈጨፉና ገዳሙም ተበዝብዞ ሲቃጠል፤ ይሄ ወንጌል ከሌላ ንብረት ጋር ተዘርፎ ከሰው ወደሰው ሲዘዋወር ቆይቶ በመጨረሻ አቡነ አብርሃም እጅ እንደገባ እና እሳቸውም በምስጢር ጠብቀው አቆይተው በሚያርፉበት ጊዜ ለሚወዷቸው የመንፈሳዊ ልጃቸው ለመምህር ሰይፈ ሥላሴ “ይኸን የንጉሠ ነገሥቱ የብፅዓት ቃል ያለበትን መጽሐፍ፤ መምጣታቸው አይቀርምና እንደገቡ አስረክብልኝ” ብለው አደራ ሰጥተው እንዳረፉ ተዘግቧል። ቤተ ክርስቲያኑም ለብዙ ጊዜ ተዘግቶ ነበር።

መምህር ሰይፈ ሥላሴም ከጠላት ወረራ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ተመልሰው ወደ ከጎጃም ወደ ርዕሰ ከተማቸው ሲጓዙ እግረ መንገዳቸውን የደብረ ሊባኖስን ገዳም ሊሳለሙ ገብተው ስለነበር አቡነ አብርሃም ‘ሰማይ ሩቅ፤ አደራ ጥብቅ’ ብለው የሰጡኝን አደራ ይረከቡኝ ብለው መጽሐፈ ወንጌሉን ለንጉሠ ነገሥቱ አቀረቡ።

ንጉሠ ነገሥቱም መጽሀፉን ወስደው ተጨማሪ ብፅዓት አክለውበት ለገዳሙ መልሰው ሰጥተውታል። ይኼም አዲስ ጽሑፍ፦ “እንደሌለህ የቆጠረህን የሙሶሊኒን ኃይል ከነሠራዊቱ የሰበርክ፤ የተጠቃችውን ኢትዮጵያን በእውነተኛ ፍርድህ የተመካችውን ያላፈርክ፤ ምስጋና ለአንተ ብቻ ይገባል፤ የአገርህን የኢትዮጵያን ነጻነት ለአንተ አደራ እላለሁ፤ እኔ እንደአባቶቼ እንግዳ ነኝ። ነሐሴ ፬ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ/ም - ቀ.ኃ.ሥ. ንጉሠ ነገሥት” ይላል.

የሕንጻው ግንባታ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ንጉሠ ነገሥቱ ለገዳሙ ሕንጻ ማሠሪያ መነሻ ይሆን ዘንድ ወጭ አድርገው ለእጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ (በኋላ አቡነ ባስልዮስ) እና ለአባ ሐና ጅማ አስረከቡ። በገንዘቡም አክሲዮን በመግዛትተና በልዩ ልዩ የልማት ሥራ ገቢ እየተደርገ ከ፲፱፻፴፬ ዓ/ም እስከ ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ድረስ ተጠራቅሞ ፩ ሚሊዮን ፪፻፳፮ሺ ፩፻፺፰ ብር ከ፺፩ ሣንቲም ስለደረሰ፤ የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ግንባታ የሥራ ጥናት ተጠናቆ ግንቦት ፳፬ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም የመሠረቱ ደንጊያ ተቀመጠ። ለሥራውም ክንውን በልዑል አልጋ ወራሽና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የሚመራ ቦርድ ተቋቋመ። የቦርዱም አባላት፦

  • ልዑል ደጃዝማች አሥራተ ካሣ (በኋላ ልዑል ራሥ)
  • ልዑል ደጃዝማች መንገሻ ሥዩም (በኋላ ልዑል ራሥ)
  • አባ ሐና ጅማ

፲፻፶፫የታኅሣሥ ግርግር በኋላ በሞት የተለዩትን አባ ሐናን በመተካት ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል እና ሊቀ-ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ የቦርዱ አባላት ሆነዋል።

ይሄ የግንባታ ቦርድ በአጥኚው ኩባንያ እየተረዳ በሥራ ሚኒስቴር መሪነት እየተቆጣጠረ ሥራውን በሚገባ አሠርቶ ካጠናቀቀ በኋላ ግንባታው በተጀመረ በሦስተኛው ዓመት ቅዳሴ ቤቱ ኅዳር ፱ ቀን ፲፱፻፶፪ ዓ/ም ተመረቀ።

የሕንፃው ፍጆታ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
  • (ሀ) ለዋናው ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥራ ------------- ፯፻፵፪ ሺ ፫፻፸፭ ብር ከ ፴፫ ሣንቲም
  • (ለ) ለልዩ ልዩ ዕቃና ለሥዕል ሥራ ------------- ፬፻፶፱ ሺ ፯፻፩ ብር ከ ፲፫ ሣንቲም
  • (ሐ)ለአጥር፣ ለድልድልና ለዕቃ ቤት ------------- ፹፰ ሺ ፱፻፲፱ ብር ከ ፹፪ ሣንቲም
  • (መ)ለእንግዶች ማረፊያና ለግቢው አስፋልት ሥራ--------- ፩፻፷፭ ሺ ፬፻፸፱ ብር ከ ፹፯ ሣንቲም
  • (ሠ)ለጥናት መቆጣጠሪያ-------------------- ፩፻፲፮ ሺ ፯፻፱ ብር ከ ፲፭ ሣንቲም
  • (ረ) ለመሐንዲሶች አበልና መጓጓዣ--------------- ፳ ሺ ብር

ጠቅላላ ድምር ---------------------------- ፩ ሚሊዮን ፭፻፺፫ ሺ ፩፻፹፭ ብር ከ ፴ ሣንቲም

የምረቃው ሥነ ሥርዓት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የደብረ ሊባኖስ ገዳም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር፤ መሳፍንት፤ መኳንንት፤ ሚኒስቴሮችና ሌሎች ባለሥልጣናት ሲገኙ፤ የአዲስ አበባ አድባራት መምህራንና ነዋሪ ሕዝብ ከሰላሌ አውራጃ ሕዝብ ጋር ተሰብስቦ፣ ከዋዜማው ጀምሮ በገዳሙ ክበብ አድሮ ነበር። ሌሊቱን ሁሉ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ከንጋቱ ፲፪ ሰዓት ሲሆን ጸሎተ ቅዳሴው ተጀመረ። የየክፍለ ሀገሩ ሊቃነ ጳጳሳት በ፫ቱ መንበር ተደልድለው ሥርዓተ ቅዳሴውን አካሂደዋል።

ከቅዳሴው በኋላ የምረቃው ሥነ ሥርዓት ሲጀመርና የሠሌዳው ጽሑፍ ሲገለጥ፤ ፳፬ ጊዜ መድፍ ተተኮሰ። ንጉሠ ነገሥቱም የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።

የጻድቁ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም በሚጠራበት በዚህ ገዳም የዛሬ ሁለት ዓመት የዚህን ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የመሠሩትን ድንጋይ ባኖርን ጊዜ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ፍጻሜውን እንዲያሳየን ተስፋችንን ገልጠን ነበር። እነሆ ሁሉን ማድረግ የሚቻለውና የለመኑትም የማይነሣ አምላክ የሕንፃውን ሥራ ተፈጽሞ ለማየት አበቃን። ይህን ላደረገልን አምላክ ከምስጋና በቀር ምን ውለታ ልንመልስለት እንችላለን? ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ወይስ ጭንቀት፤ ወይስ ረኀብ፤ ወይም ራቁትነት ነው?” ብሎ የተናገረውን ቃል ተመልክተው የሐዋርያነት ተግባራቸውን የፈጸሙ፣ ከፍ ያለ ተጋድሎ እና ትሩፋት የሠሩ የክርስትና ዓምድ እንደነበሩ የታመነ ነው። ከሳቸውም ‘የቆብ ልጅ’ ሆነው የታወቁት ገዳማት ብዙ ናቸው። በያለበት ልጆቻቸው ያስተማሩትም ከፍ ያለ ቁጥር ነው። ኢትዮጵያ በአረመኔነትና በእስልምና እንዳትዋጥ አሥግቶ በነበረበት በዚያን ዘመን እርሳቸውና እርሳቸውን የመሳሰሉት ሐዋርያት በሰጡት አገልግሎት ምክንያት ኢትዮጵያ ‘የክርስትና ደሴት’ ተብላ ተጠርታበታለች። ይህን አጋጣሚ ጊዜ ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ጳጳሳትና የቤተ ክህነት መምህራን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን አርአያነት በመከተል የክርስትናን ሃይማኖት ለማስፋፋት ድካማቸውን ባለመቆጠብ፣ ራሳቸውን ለዚህ ታላቅ ሐዋርያዊ ተግባር መሥዋዕት በማድረግ እንዲሠሩና እንዲያሠሩ ልናሳስባቸው እንወዳለን። ወንድም ለወንድሙ ከዚህ የበለጠ ትሩፋት ሊሠራለት አይችልም። እኛም በዚህ ገዳም አምላከ ተክለ ሃይማኖት ይህን ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊ እቅድ ለማሠራት እንዲያበቃን ብፅዓት አቅርበንለት ነበር። ልመናችንን ሰምቶ ብፅዓታችንን ስለፈጸመልን ለአምላካችን ክብር ምስጋና ይግባው። የሕንፃውን ሥራ እየተቆጣጠረ በሚገባ ለማስፈጸም አደራችንን የጣልንበት በብፁዕ አባታችን አቡነ ባስልዮስ እና በተወደደው ልጃችን በልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ፕሬዚዳንትነት የሚመራው ቦርድ አባሎች ሥራውን በመልካም ስላስፈጸሙ ከልብ እናመሰግናቸዋለን። ወደፊትም ለዚህ ቤተ ክርስቲያን ንጽሕናና መልካም አጠባበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ አደራችንን ለፕሬዚዳንቱና ለቦርዱ አባሎች ጥለነዋል። በዚህ ገዳም በጻድቁ ስም ለተሰበሰቡት ምእመናንና አገልጋዮች የግዚአብሔር ረድኤትና የጻድቁ በረከት እንዳይለያቸው እንለምናለን።”

በዚህ ዕለት ግምታቸው ሰባ ሺ ብር የሆነ የፋርስ ምንጣፎች በያይነቱ፤ ወርቀ ዘቦ እና ሙካሽ ሥራ ልብሰ ተክህኖ ለ፯ቱ ልዑካን የ ፫ ጊዜ ቅያሪ ሲሰጥ፤ ልዩ ልዩ ንውያተ ቅድስታም እንዲሁ ተሰጥተዋል።

በአሁኑ ዘመን

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በአሁኑ ዘመን፣ ደብረ ሊባኖስ ከ240 በላይ መነኮሳትን ሲያስተናግድ፣ ከዚህ በላይ ብዛት ያላቸውን ምዕመንና ተማላጆችን እንዲሁም ለማኞችን ያስተዳድራል። ገዳሙ በጥንቱ ዘመን ስርዓት መሰረት በመጋቢ የሚመራ ሲሆን ፣ ይህ መጋቢ መነኮሳቱን ለመወከል በተውጣጡ 12 ተወካዮች ላይ ሸንጎ ይይዛል።

  1. ^ walis Budge. The life and Miracles of Takla Haymanot in the version of Dabra Libanos, London 1906, 195- 265
  2. ^ የአጼ ዘርአ ያዕቆብ ዜና መዋዕል
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሐዋርያዊ ድርጅት፣ “ትንሣኤ፡ የሃያ አምስት ዓመታት መንፈሳዊ እርምጃ” (፲፱፻፶፱ ዓ/ም) ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት።